ቀጥታ፡

ለአምስት የህክምና ተቋማት የፍተሻ ወሰን አክሪዲቴሸን አገልግሎት ተሰጠ

 አዲስ አበባ መጋቢት  21/2013  ( ኢዜአ) ለአምስት ህክምና ተቋማት የፍተሻ ወሰን የአክሪዲቴሸን አገልግሎት መስጠቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሪዲቴሽን ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

አገልግሎቱ የተሰጠው በማይክሮ ባዮሎጂ፣ በክሊኒካል ኬሚስትሪና በሔማቶሎጂ መስኮች ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሪዲቴሽን ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው አገልግሎቱን ያገኙት ተቋማት በውስን የፍተሻ ወሰኖች ላይ የሚሰጡትን አገልግሎት ወደ ሌሎች ያሰፉታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የአርመን ሀንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ቡታጅራ ጠቅላላ ሆስፒታልና ወራቤ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስቲታል በማይክሮ ባዮሎጂ የፍተሻ ወሰን የአክሪዲቴሽን አገልግሎት ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ ይህም ቲቢን ለመመርመር ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

ቀሪዎቹ ሁለቱ ተቋማት ደግሞ በክሊኒካል ኬሚስትሪና በሔማቶሎጂ የፍተሻ ወሰን የአክሪዲቴሽን ተጠቃሚ መሆናቸውንም ገልጿል፡፡  

ተቋማቱ አክሪዲቴሽን ባገኙባቸው ወሰኖች ለህብረተሰቡ ትክክለኛና ተዓማኒነት ያለው እንዲሁም ጊዜውን የጠበቀ አገልግሎት እንደሚሰጡ ተጠቅሷል፡፡  

ሌሎች ወደ አክሪዲቴሸን ያልመጡ ተቋማትም ለህብረተሰቡ በሚሰጡት አገልግሎት ተመራጭና ተዓማኒ እንደሚያደርጋቸው የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያሳያል፡፡

ጽህፈት ቤቱ በተያዘው በጀት ዓመት ለ61 ተቋማት የህክምና ላቦራቶሪ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡

የአክሪዲቴሽን የህክምና ላቦራቶሪ አገልግሎት ያገኙት የአርመን ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት፣ ቡታጅራ ጠቅላላ ሆስፒታል፣ ወራቤ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ግሩም አጠቃላይ ሆስፒታልና ተክለሃይማት አጠቃላይ ሆስፒታል ናቸው፡፡

ሰባት ተቋማት ደግሞ የዘረጉትን አክሪዲቴሽን አስጠብቀው ባለመቀጠላቸው አክሪዲቴሽን በጊዜያዊነት የታገደባቸውሲሆን፣ የአራት ተቋማት እግድ ግን መነሳቱን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም