ተቋማቱ በቁጥጥር የተለዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል- የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማቱ በቁጥጥር የተለዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል- የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም
አዳማ መጋቢት 21 / 2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲስ አበባ ሪጂን በቁጥጥር ለተለዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚገባቸው የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አሳሰበ።
ተቋሙ በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣንና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲስ አበባ ሪጂን ላይ በመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በተለዩ ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።
የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በህግ የተደነገጉ የሰዎች መብቶችና ጥቅሞች ከአስፈፃሚ አካላት መከበራቸውን በማረጋገጥ የህግ የበላይነትን መሰረት ያደረገ ጥራት ቅልጥፍናና ግልጽነት ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲዘረጋ ይሰራል።
ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠውን ሃላፊነት መሰረት በማድረግ በአስፈጻሚ አካላት ላይ የቁጥጥር ስራን በመስራት መፍትሄን ያመለክታል።
ዛሬ በአዳማ በነበረው የውይይት መድረክ ተቋሙ በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ላይ ባደረገው የቁጥጥር ስራ ግኝቶችን ያቀረቡት በተቋሙ የአስተዳደር በደል መቆጣጠር ዳይሬክተር አቶ አዳነ በላይ ናቸው።
ሰፊ የደንበኞች ቅሬታ ከሚነሳባቸው ተቋማት የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አንዱ መሆኑን ያወሱት አቶ አዳነ ባለስልጣኑ ሰፊ ክፍተቶች ቢኖሩበትም በበጎ የሚነሱ ተግባራት እንዳሉትም ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ በውሃ ተደራሽነት፣ በፈረቃ ካርታ ዝግጅት፣ ከደንበኛ ፎረም ጋር አብሮ መስራት እንዲሁም ውስጥና የውጭ ቅሬታ አፈታት በመልካም ጎን የሚነሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
"የውሃ እጥረትና ብክነት፣ የቅንጅታዊ አሰራር ጉድለት፣ የዘመናዊ ፍሳሽ ማስወገጃ እጥረትና በሰራተኞች ዲሲፕሊን በኩል ለሚነሱ ክፍተቶች ደግሞ ባለስልጣኑ አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጣቸው የሚገቡ ናቸው" ብለዋል።
"በተለይም የውሃ ሽፋን በሌለባቸው ቦታዎች የሚቀርቡ ሪፖርቶች እርምት ሊወሰድባቸው ይገባል" ሲሉ አመልክተዋል።
በአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አገልገሎት አሰጣጥ የተደረገ የቁጥጥር ግኝት ያቀረቡት ደግሞ በህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የትምህርትና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ተመስገን ወልደ ኪዳን ናቸው።
እንደ አቶ ተመስገን ገለጻ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ አዲስ አበባ ሪጂን ራሱን ችሎ መቋቋሙ፣ የስነምግባር ግድፈት ባሳዩት ሰራተኞች ላይ አስተማሪ እርምጃ መውሰዱና ትራንስፎርመር በሀገር ውስጥ ማምረት መጀመሩ በመልካም ጎኑ የሚጠቀሱ ተግባራት ናቸው ።
ከፍተኛ የግብአት እጥረት፣ የጥራት ጉድለትና ብልሽት፣ ለቆጣሪ ፍላጎት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ አለመስጠትና በክፍያ አሰባሰብ የደንበኞች እንግልት ደግሞ በኤሌክትሪክ አገልግሎቱ የደንበኛን ቅሬታ ያባባሱ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የሴቶች ህጻናት አካል ጉዳተኞች እንባ ጠባቂ ወይዘሮ ሳኒያ ሳኒ በበኩላቸው አገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ በቁጥጥር ለተለዩ ግኝቶች ፈጥኖ ምላሽ በመስጠት መልካም አስተዳደር ማስፈን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል ።
በቁጥጥር የተለዩ ግኝቶች የቀረበባቸው ሁለቱ ተቋማት በበኩላቸው ለተነሱት ክፍተቶች መፍትሔ መስጠት የሚያስችሉ የአሰራር ማሻሸያዎች ላይ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የዲስትሪቢዩሽን ሲስተም ቴክኒክ ሃላፊ አቶ ጥላሁን ብርሃኑ እንዳሉት ተቋማቸው ከህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ግኝት አስቀድሞ የደንበኞችን ቅሬታ በሚፈቱ የአሰራር ማሻሻያዎች ላይ እየሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የደንበኞች አገልግሎት አብይ የስራ ሂደት ሃላፊ ወይዘሮ በዕድልሽ ሃይለማሪያም በበኩላቸው ባለስልጣኑ ከስራ እቅዱ ጀምሮ ከደንበኞች ፎረም ጋር መስራቱ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት እንደረዳው ተናግረዋል።
የኢትየጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በኢ.ፈ.ድ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ 15 መሰረት በተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 211/1992 የተቋቋመና ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1142/2011 መሰረት የተቋቋመ የዴሞክራሲ ግንባታ ተቋም ነው።