አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ የንግድ መገናኛ ብዙኃንን የሚያስፋፋ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ የንግድ መገናኛ ብዙኃንን የሚያስፋፋ ነው
አዲስ አበባ መጋቢት 21/2013/ኢዜአ/ አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ የንግድ ሚዲያ (መገናኛ ብዙኃንን) የሚያስፋፋ መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ገለጸ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ''በኢትዮጵያ የሚዲያ ፖሊሲ ዋና ዋና ሃሳቦች እና በማስታወቂያ ስርጭት የባለደርሻ አካላት ሚና በሚል '' ርዕስ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ተወያይቷል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግዛው ተስፋዬ በውይይቱ የመነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በአገሪቷ ራሱን የቻለ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ የወጣው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ 22 የሚሆኑ የፖሊሲ ውሳኔዎችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።
ፖሊሲው የመገናኛ ብዙኃንን ከመስፋፋትና የመገናኛ ብዙሃን ባለቤትነትን ከመጨመር አኳያ ሰፊ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ፖሊሲው ከጸደቀ ጊዜ ጀምሮ ፖሊሲውን መነሻ ያደረጉ ህጎችና ዝርዝር ማስፈጸሚያዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸው፣ በዓዋጅ ደረጃ ጸድቀው ዝርዝር መመሪያዎች በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ይህም ከዚህ ቀደም የነበረውን የአገሪቷን የመገናኛ ብዙኃን ይዘት ስብጥርና ባለቤትነት ይቀይራል ብለዋል።
መንግሥት ለንግድና ለማህበረሰብ መገናኛ ብዙኃን የሚደረግ ቀጥተኛ ድጋፍ ሳያደርግ መቆየቱንም ተናግረዋል።
ፖሊሲው የንግድ ሚዲያ ለመደገፍ ፣ በመገናኛ ብዙኃን ላይ የተጣለውን የገቢ ቀረጥ መቀነስ፣ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ መስጠት፣ የመስሪያ ቦታ፣ የብድር፣ የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ ዕድል እንደሚያመቻች አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ሥራአስፈጻሚ አቶ አማረ አረጋዊ በበኩላቸው ፖሊሲው በቀጥታ ተግባራዊ መደረግ ሲጀመር በተለይ ለንግድ ሚዲያ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።
በዚህም የንግድ ሚዲያ በባለቤትነት በስፋት የሚሳተፉበትን ሁኔታ እንደሚያበረታታ ገልጸዋል።
ፖሊሲው ከዚህ ቀደም የነበሩ የማስታቂያ ሕጎችን አሻሽሏቸዋል።
በሕዝብና በንግድ ሚዲያ በአንድ ሰዓት ውስጥ እኩል 12 ደቂቃ የማስታወቂያ ጊዜ የነበረው ጊዜ ተቀይሮ በንግድ ሚዲያ ላይ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጥ ይፈቅዳል።
በውይይቱ የተሳተፉ የማስታወቂያ ደርጅቶች ባለቤቶች የማስታወቂያ መሳሪዎች ከውጭ በሚገባበት ወቅት ያለው ከፍተኛ ቀረጥ ጫና እያሳደረባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ለዘርፉ የሚደረገው ማበረታቻ ችግሮቻቸውን ይፈታል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።