እንደዋዛ ወጥተው የሚቀሩት "የበረሃው ሲሳዮች" - ኢዜአ አማርኛ
እንደዋዛ ወጥተው የሚቀሩት "የበረሃው ሲሳዮች"
በቁምልኝ አያሌው (ኢዜአ)
ዓለም አቀፉ የፍልሰተኛች ድርጅት በቅርቡ ባዘጋጀው ጉብኝት ለመሳተፍ ወደ ድሬዳዋና ጅቡቲ የመጓዝ እድሉ ገጥሞኛል።
በጉብኝቱ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ ባለሙያዎች መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት መውጫና መግቢያ ስፍራዎችን ተመልክተዋል።
መዳረሻውን ድሬዳዋ ባደረገው ጉብኝት በመጀመሪያው ቀን ፍልሰትና የፍልሰትን ውስብስብና አስቸጋሪነት የሚመለከት ስልጠና ተሰጥቶበታል።
ስልጠናው ኢትዮጵያዊያን ያላዩትን ህልም ለማሳካት መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን አማራጭ በማድረግ ሲጓዙ የሚገጥሟቸውን አስቸጋሪ የህይወት ውጣ ውረዶች ያመላከተን ነበር።
በሁለተኛው ቀን የተያዘውን ጉብኝት ለማካሄድ ደግሞ ቀጠሮ ይዘን ተለያየን።
ምሽቱን የበረሃዋ ንግሥት በሆነችው ድሬ ቀኑን ሙሉ ከዋለባት ሐሩር ዕረፍት ያገኘች ትመስላለች።እንደ እንፋሎት የሚጋረፈው ሙቀትም በመጠኑ ቀንሶ ነፋሻ አየር እያገኘን ወደ ማረፊያችን ሄድን።
በከተማዋ ታሪካዊና ጥንታዊ ዛፎች መኖሪያቸውን ያደረጉ አዕዋፋትም መንጋቱን ለማብሰር የሚያሰሙት ዝማሬ እያጀበን ስልክ እየተደዋወልን መሰባሰብ ጀመርን።ወደምንጎበኘው ሥፍራ ለመጓዝ።
መንገደኞቹ ጋዜጠኞች ጎናቸውን ለማሳረፍ ከያዛቸው ሆቴሎች በመውጣት በተዘጋጁላቸው ተሽከርካሪዎች ገቡ። ጉዞው ወደ ከተማዋ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ ሆነ።
ጉዞው የተሳካና ሰላማዊ እንዲሆን ተጓዦች ለፈጣሪያቸው ፀሎታቸውን እያደረሱ ፀሐይ ስትወጣ እያየን ጉዞውን ቀጠልን። ሰማዩም የፀሐይዋን መውጣት ለማብሰር ያሰበ ይመስል ማብረቅረቅ ጀምሯል።
ሁሉም ተጓዦች ግራ ቀኛቸውን በመቃኘት የአካባቢውን መልካአ ምድር በአግራሞት እየተመለከቱ ጉዞው ዝምታ ቢሰፍንበትም፤ፀሐይ የዘወትር ተፈጥሯዊ ዑደቷን ለማሳየት ፈገግ ብላለች።
አካባቢው እርጥበት የተጠማ መሆኑን በሚያሳብቀው መሬት የተሰራውን አስፋልት ይዞ ቀጥሏል። እንደ ወጭት በተንጋለለው ሥፍራ የወጣችው ፀሐይ ከምድር እንጂ ከሰማይ ስለመውጣቷ መጠራጠር የጀመርነው ጉዞው ሲረዝም ነበር።
በሶማሌ ክልል የደወሌ ጠረፍን እያቋረጡ ጅቡቲ ለመግባት የሚጥሩ ኢትዮጵያዊንን መውጫና መግቢያ ለመመልከት እየተቃረብን ነው።
በሥፍራው የተመደቡ የመንግሥት የጸጥታ አካላት አስቁመው ጥያቄዎች ካቀረቡላቸው በኋላ ተጓዦቹንና የጉዞውን ዓላማ ሲያውቁ ''ይለፍ'' ይሰጡናል።
የሶማሌ ማህበረሰብ ባህላዊ ቤቶችንና በዙሪያቸውም የቤት እንስሳት ይስተዋላሉ። አይሻ በምትባለው የወረዳ ከተማ እስክንደርስ አራዋ፣ ሚሎ፣ አንዶቤድ፣ አዲጋላ፣ ማሊክ፣ ላሳራትና ሌሎችም አነስተኛ መንደሮችን አቆራርጠን አልፈናል።
አይሻ "በምድረ በዳ እንደተገኘች የኤደን ፍሬ" ትመስላለች። በሽንሌ ዞን የምትገኘው ከተማ ዛፎች የሞሉባት በመሆኗ የአየር ንብረቷም ነፋሻማ ነው። አይሻ በሶማሊኛ ቋንቋ ጥጋብ ማለት መሆኑም ተነግሮናል።
ታዲያ አይሻን አቋርጠው ወደ ጅቡቲ ለመሸጋገር ለአስቸጋሪ ሕይወት የሚዳርጉ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ አነጋጋሪ አድርጓታል። መዳረሻቸውን እንኳን በቅጡ ሳያውቁ መነሻቸውን ከትግራይ፣ ከአማራና ኦሮሚያ ክልሎች አድርገው በረሃውን እያቆራረጡ የሚያልፉት በዚህች ወረዳ በኩል ነው።
የመከራውን ጉዞ አልፈው ከሚመኙት ግን ከማያውቁት ሥፍራ ሲደርሱ ከመራብና ከመጠማት በላይ፤ በዱር እንስሳት ተበልተው ሕይወታቸውን የሚያጡት ዜጎች ቁጥር ለመገመት እንደሚቸገሩ የሥራ ኃላፊዎች ይናገራሉ።
በትራንስፖርት የሚያልፉ ፍልሰተኞችን ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፤ በተለያዩ አቅጣጫዎች በእግር የሚያልፉትን ማስቆም እንደሚያስቸግራቸውም ይገልጻሉ። ፍልሰቱን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ከስፋቱና ውስብስብነቱ ጋር ተያይዞ ''ከባድ'' እንደሆነም ጠቁመዋል።
ደላሎች አብዛኛዎቹ ፍልሰተኞች በእግር፣ ቀሪዎቹን በተሽከርካሪዎች በሌሊት ካመጡ በኋላ የከተማ መብራት በማሳየት ''ከኢትዮጵያ ሳይወጡ ጅቡቲ ደርሳችኋል'' በሚል በረሃ ላይ በትነዋቸው ይሄዳሉ።
ፍልሰተኞቹ ከማያውቁትና ከማይደርሱበት የተስፋ መዳረሻ ደርሰናል ብለው ነግቶ ሲያዩና አሁንም በኢትዮጵያ ምድር መገኘታቸውን ሲያውቁ መታለላቸው ይገባቸዋል።
በአካባቢው የስልክ ኔትወርክ አለመኖር ደግሞ በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ በመሆን የቁጥጥር ስራውን አስቸጋሪ አድርጎታል። ከባቢያዊ ቅኝት የሚያደርጉ የጸጥታ አካላትም በየጊዜው የሚያገኙትን አስከሬን ቀብረው ይመጣሉ።
በአይሻ የነበረውን ቆይታ አጠናቀን ወደ ደወሌ ጉዞአችንን ቀጥለናል።
የፀሐዩ ሃሩር ወላፈን መጋረፉን ቀጥሏል፤ የተንጋለለው መሬት በርቀት ሲታይ ከሰማይ ጋር የተሳሰረ ይመስላል። ከዚህ የባሰ ምን ችግር ቢገጥም ነው? ይህን ጸሃይ እንደ እሳት የሚነድበትን በርሃ አቆራርጦ ወደ ማያውቁት አገር ለመዳረስ መሻትም ያስብላል።
እውነት ግን ኢትዮጵያ ተሰርቶ የሚለወጥባት አገር ሆና የማያውቁትን አገር በመናፈቅ በበረሃ መሞት ምርጫ ተደረገ? የተሻለ ኑሮ ለማግኘት ቢታሰብ እንኳን ስለምን መደበኛ ፍልሰትን ምርጫ ማድረግ አልተቻለም? ህጋዊ ሰነድ አሟልቶ ከአገር ለመውጣትስ አልታሰበም? እያልኩ ራሴን እጠይቅ ጀመር።
በቅርብ ርቀት ወደ ጅቡቲ አቅጣጫ ከሰማዩ ሐሩር ከምድሩ ግለት ጋር በመታገል መዳረሻቸው የራቃቸውና በድካም ተውጠው ግራ የተጋቡ ፍልሰተኞች አልፎ አልፎ ሲጓዙ ይስተዋላል።
ከጅቡቲ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ደወሌ ደረስ የኢትዮ-ጅቡቲ የድንበር ምልክቶች በግራና ቀኝ ቆመው ይታያሉ።
ወደ ሁለቱም አገሮች የሚወጡና የሚገቡ የጭነት ተሽከርካሪዎች የፍተሻ ወረፋ በመጠባበቅ በረድፍ ተሰልፈዋል። በአካባቢው ተንቀሳቅሶ ነገሮችን ለመረዳት ፈቃድ ጠይቆ ማግኘት ግዴታ ነው።ተፈቀደልንም።
በኢትዮጵያ በኩል ተመላሽ ፍልሰተኞች የሚቆዩበት ማዕከል አለ።ማዕከሉ መደበኛ ባልሆነ መንገድ በረሃውን አቋርጠው ሲጓዙ በጅቡቲ የጸጥታ ኃይሎች ተይዘው የሚመለሱ ኢትዮጵያዊያን ይርፉበታል።
ተመላሾቹ በሕመም፣ በድካም፣ በረሃብና በውሃ ጥምና የጠወለጉ ፊቶች ይስተዋሉባቸዋል። ዳሩ ግን የምግብም ሆነ መጠጥ ይሉት ሕክምና አገልግሎት ሲያገኙ አይስተዋልም። ሴቶችና የእናት እቅፍ ያልጠገቡ ህጻናትም የገፈቱ ቀማሽ ናቸው።
ኢዜአ በሥፍራው ያነጋገራቸው ተመላሾች እንደሚሉት ባህር ማዶ በመሻገር በቀላሉ የተሻለ ገንዘብ ማግኘት እንደሚቻል በመስማት ብቻ አስቸጋሪውን ጉዞ ተጋፍጠዋል።
ከመነሻቸው ጅቡቲ እስኪደርሱ ድረስ ለደላላ ''ቀላል የማይባል'' ገንዘብ መክፈላቸውንም ተናግረዋል።
ከአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ሃብሩ ወረዳ ያደረገችው የ20 ዓመቷ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ወጣት መሬም ዳውድም ይህኑ ነው ያለችው። የማታውቀውን ህልም በመሻት ባደረገችው ጉዞ ከገንዘቡ ባለፈ የደረሰባትን መከራ ስታስታውስ እንባ በዓይኗ ያቅራል።
በጉዟቸው የደረሰባቸውን ግርፋት፣ እስርና ስቃይ ስትገልጽም እንባዋ ይተናነቃታል።
አስቸጋሪውን ጉዞ ለመጀመርም ዕድል ቀንቷቸው ባህር ማዶ የተሻገሩ የተሻለ ገቢ አግኝተዋል የሚለው ሃሳብ እንዳነሳሳት ገልጻለች።''ትርፋችን ግን የህይወትን መከራ መጋፈጥ ሆነ'' ትላለች።
ከማዕከሉ የሚሰማው የህጻናቱ ''ውሃ አጠጡን ምግብ ስጡን'' ጩኸት ውስጥን ይረብሻል።
በረሃን ለማቋረጥ ሲሞክሩ በድጋሚ የተያዙ ፍልሰተኞች ጉዳይ መስማ ከምንም በላይ አግራሞትን የሚያጭር ጉዳይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ከኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን በማድረግ ወደ ሥፍራው እንዳቀና የሚናገረው የ18 ዓመቱ ወጣት ለማ አያና፤ የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቀቆ ስራ ማግኘት ስላልቻለ በኢ-መደበኛ መንገድ ባህር ማዶ ለመሻገር መሻቱን ገልጿል።
ወደ ቤተሰቦቹ ተመልሶ ለመኖር ፍላጎት ቢኖረውም ምንም ዓይነት ገንዘብ ሳይዝ ለመመለስ ህይወት ጨለማ እንደሆነችበት ይናገራል።
የዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት በኢትዮጵያ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ታደለ አካሉ ዜጎች በአገራቸው ህጋዊ ሰነዶችን አሟልተው ከአገር መውጣት እንዳለባቸው ይመክራሉ።
መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላትም ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የመገናኛ ብዙኃንም መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ትኩረት እንዲሰጠው ከቃላት አጠቃቀም ጀምሮ የሕገ ወጥ ፍልሰት አስከፊነትን ማሳየት አለባቸው ይላሉ።
ኢትዮጵያዊያን ሆይ! ቢቻላችሁ በአገራችሁ ሰርታችሁ ለመለወጥ ሞክሩ። እንደዋዛ ወጥቶ "የበረሃ ሲሳይ" ሆኖ መቅረት ሊበቃን ይገባል።
መደበኛው ያልሆነ ፍልሰት የተስፋ ሕልም አንግቦ በቅርብ መቅረት ነውና ህይወትን የበረሃ ሲሳይ አድርጎ በሕይወት ከመፍረድ እንታቀብ! እላለሁ።
ቸር ያሰማን!! ሰላም ለአገሬ ልጆች ሁሉ!!