የአፍሪካን በአፍሪካ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካን በአፍሪካ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21/2013 ( ኢዜአ) የአፍሪካን በአፍሪካ በአብዱራህማን ናስር
አፍሪካውያን ነፃነታቸውን ካረጋገጡ በኋላ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመሰረቱት ለመረዳዳት፣ ለመደጋገፍና አብሮ ለመልማት ብሎም የሚያጋጥማቸውን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት በማሰብ ነው። የህብረቱ አባል ሀገራት “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች” በሚል መርህ ላይ በመመስረት ተመካክረውና ተራርመው በጋራ የመስራት ባህላቸውን ለማጎልበት እየሰሩ ይገኛል።
የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ቴሪ ሜይስ “African Solutions for African Problems: The Changing Face of African-Mandated Peace Operations” በሚል ርእስ በፃፉት ጽሑፍ ላይ “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች” የሚለው መርህ ዓላማው የአፍሪካ ሀገሮች የራሳቸውን ችግሮች በራሳቸው መፍታት እና በአህጉራዊ ጉዳዮች ውስጥ የውጭ ተዋንያን ተጽዕኖን ለመቀነስ መሆኑን ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን እንዲፈቱ ጽኑ አቋም ካላቸው ግንባር ቀደም ሀገራት አንዷ ነች። የታሪክ ምሁራን እንደሚገልጹት ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት በማድረግ ረገድ ወሳኝ ድርሻ አበርክታለች። አፍሪካውያን በወንድማማችነትና በአንድነት በመሆን ለጋራ ዕድገት እንዲሰሩ ብሎም ችግሮቻቸውን በራሳቸው እንዲፈቱ ኢትዮጵያ የተጫወተችው ሚናም ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤትም ይሁን ከሌሎች ሀገራት ጋር በወዳጅነትና በትብብር የመስራት እና አብሮ የመልማት የቆየ ባህል ያላት ሀገር ነች። ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳ ባላት አቅም ሁሉ ሌሎችን ለመርዳት ጥረት ከማድረግ ባለፈ የትኛውንም ሀገር ተንኩሳ አታውቅም። ይልቁንም ከሀገራት ጋር ባላት ጠንካራ ወዳጅነት፣ ሽብርተኝነትን በመዋጋት፣ ሰላምን በማስከበር ተልእኮዋ ትታወቃለች። ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋር አብሮ ለመልማት የተለያዩ ግዙፍ የመሰረተ ልማት ትስስርን ለማጠናከር ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ፕሮጀክቶችን እየተገበረች ትገኛለች። ከእነዚህ ግዙፍ መሰረተ ልማቶች መካከል አንዱ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው።
ታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ከመጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ግብጽ እና ሱዳን በሚያነሷቸው አወዛጋቢና ተለዋዋጭ አቤቱታዎች ምክንያት ለበርካታ ጊዜያት ውይይቶችና ምክክሮች የተካሄዱ ቢሆንም እስካሁን በውሃ ሙሌትና ኦፕሬሽን ዙሪያ መቋጫ ላይ አልተደረሰም። ኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብ የሶስቱ ሀገራት በጋራ የመልማት ፍላጎት የሚደግፍ እንጂ ፈፅሞ ጉዳት እንደማያስከትል በተደጋጋሚ ብትገልጽም ሁለቱ ሀገራት ከመቃወም ቦዝነው አያውቁም።
በተለይ ግብጻውያን “የናይል ወንዝ ከፈጣሪ የተሰጠን ስጦታ ነው፣ የውሃው ባለቤቶችም እኛ ነን” እስከማለት የደረሰ አቋም በመያዝ በአባይ ወንዝ ላይ ምንም ዓይነት ልማት እንዳይሰራ ለዘመናት ሲገዳደሩ ኖረዋል። የቀድሞው የግብጽ ፕሬዝዳንት መሀመድ ሙርሲ እ.አ.አ በ2013 በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት በተላለፈ ውይይት የአባይ ወንዝ የጠብታ ያህል ከቀነሰ ሁሉንም አማራጭ እርምጃዎች ለመውሰድ እንደሚገደዱ ነበር የተናገሩት። በዚያን ወቅት የአሁኑ የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ የአገሪቱ የጦር አዛዥ ነበሩ። እናም የህዳሴው ግድብ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ይህ አስተሳሰብ እንደቀጠለ መሆኑን የሚያሳዩ የተለያዩ መገለጫዎች ይስተዋላሉ። ለማሳያ ያህል ባለፈው ዓመት የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት እንዳይከናወን ከፍተኛ ትንቅንቅ ገጥመው ነበር። ምንም እንኳ የውሃ ሙሌቱ የተከናወነው በክረምት ዝናብ ወቅት ቢሆንም “ውሃችን ተነካ” የሚል ከፍተኛ እሮሮ አሰምተዋል። ዘንድሮም በተመሳሳይ የክረምት ዝናብ የሚፈጥረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ሁለተኛውን ዙር ውሃ ለመሙላት የሚደረገውን ዝግጅት ለማደናቀፍ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ በሰሞኑ ለፓርላማ ባቀረቡት ማብራሪያ “የኢትዮጵያ መንግስት የአባይን ውሃ ባለፈውም አልገደበም በሚቀጥለውም አይገድብም። የተከለከልነው ዝናብ አትገድቡ ተብለን ነው። የአባይን ውሃ ብንገድብማ ዛሬ አባይ አይፈስም ነበር። ነገር ግን ፍሰቱን አላቆመም። ከጣና የሚሄደው ውሃ እንደወትሮው እየፈሰሰ ነው። እኛ እያልን ያለነው ክረምት ላይ ዝናብ ሲዘንብ እጅግ ቢበዛ 5 በመቶ ከሚፈሰው ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው። ጣናን አትጠቀሙ ተብለን፤ ዝናብም አትጠቀሙም ከተባለ ይህ ይከብዳል።” በማለት ነበር የገለጹት።
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በርካታ የዘርፉ ምሁራን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዝናብ ውሃ የምታገኝበትን የክረምት ወቅት በመጠቀም የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት መከናወኑ በወንዙ ፍሰት ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ አለመኖሩን በመጥቀስ ግብጽ የምትስነዝረው ማስፈራሪያና ዛቻ ትርጉም የለውም በማለት ይገልጻሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት የህዳሴ ግድብ ሙሌት ግብጽንም ሆነ ሱዳንን ሊጎዳ አይችልም። የባለፈው ዓመት የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በመከናወኑ ጠቀሜታው ጎልቶ ታይቷል በማለት ያብራራሉ። ተጨማሪ የውሃ ሙሌት ከተደረገ እንዲሁ ተጨማሪ ውሃ እንደሚያገኙ የሚገልጹት ፕሮፌሰር ያዕቆብ ግብጽ እና ሱዳን ውሃ ይቀንሳል፤ ህዝባችን ይጎዳል በማለት የሚያቀርቡት አቤቱታ ለሚሰማቸው ብሎም ለሚያምናቸው አካል መግለጫ ካልሆነ በስተቀር እነርሱን የሚጎዳ ነገር እስካሁን ድረስ የለም በማለት አብራርተዋል።
ሱዳናውያን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት በተወሰነ ደረጃ ስጋታቸውን ከመናገር በስተቀር ጠንከር ያለ ተቃውሞ አልነበራቸውም። የውሃ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት የህዳሴው ግድብ ግንባታ ለሱዳናውያን የፖለቲካ ውሳኔ ሳይሆን የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ነው። ከግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኙ መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያዎች ይህም ኢንዱስትሪዎቻቸውን እንደሚያነቃቃና የግብርና ሥራዎቻቸውን ለማስፋፋት እንደሚረዳቸው ከሁሉም በላይ ደግሞ ግድቡ ከጎርፍ አደጋ እንደሚታደጋቸው ይገልጻሉ። ለዚህም ነው ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ ግብፅ በሱዳን ላይ በተለያየ መንገድ ከፍተኛ ጫና ብታሳድርባትም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በድርድር ሂደት በአብዛኛው የኢትዮጵያን አቋም ስትደግፍ የቆየችው።
ይሁን እንጂ ሱዳን በዚህ ዓመት ከግብጽ ጋር ጥምረት መፍጠሯ ብዙዎችን አስገርሟል። ከኋላ ታሪካቸው በመነሳት የሁለቱ ሀገራት የሰሞኑ ጥምረት ዘለቄታ እንደማይኖረው ብዙዎች ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። ይህ በሂደት የሚታይ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ሱዳንና ግብጽ ወታደራዊ ስምምነቶችን ፈጽመዋል። የሁለቱ ሀገራት መሪዎች አንድ ጊዜ ካርቱም ሌላ ጊዜ ደግሞ ካይሮ በመመላለስ በህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ዙሪያ መክረዋል፤ የተለያየ ዕቅድም ነድፈዋል። ኢትዮጵያ ሙሉ ትኩረቷን በትግራይ ክልል ባደረገችበት ወቅት የሱዳን ጦር በድንበር አካባቢ የሚኖሩትን የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በማፈናቀልና ንብረታቸው ላይ ጉዳት በማድረስ አካባቢውን ተቆጣጥረዋል። ለዚህም የግብጽ የሞራል ድጋፍ ከፍተኛ ነበር።
ሁለቱ አገራት ቀደም ሲል በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ሲካሄድ የነበረው ድርድር ሳይቋጭ አዲስ ሀሳብ በማምጣት ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲያደራድሩ ጠይቀዋል። ሁለቱም ሀገራት ኢትዮጵያ አስገዳጅ ህግ ካልፈረመች በስተቀር የውሃ ሙሌቱ “ህዝባችንን አደጋ ላይ የሚጥል ስጋት ደቅኖብናል” በማለት የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት እንዳይከናወን ዓለም አቀፋዊና ቀጠናዊ ተጽእኖ ለማሳደር ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። በርግጥ ጥያቄያቸው በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት አላገኘም። ኢትዮጵያ የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካ መፍታት በሚለው መርህ ላይ እንደጸናች ትገኛለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ ከሰሞኑ ሱዳን ከግብጽ ጋር የፈጠረችው ጥምረት የሱዳንን ህዝብ ባህርይ የሚገልጽ አይደለም በማለት ነበር የገለጹት። የሱዳንና የኢትዮጵያ ህዝቦች ወንድማማች መሆናቸውንም አክለው ገልጸዋል። እንደዲያውም ሱዳን የሚለው ቃል በአረብኛ እና ኢትዮጵያ የሚለው ቃል በግሪክኛ አንድ ትርጉም እንዳለው በማብራራት ኢትዮጵያን ከሱዳን፤ ሱዳንን ከኢትዮጵያ ነጥሎ ማየት አይቻልም ብለዋል።
የግድቡ የውሃ ሙሌት በተመለከተም “ኢትዮጵያ ግብጽንም ሱዳንንም የመጉዳት ፍላጎት ፈጽሞ የላትም። ኢትዮጵያ እነዚህ ሀገራት ሳይጎዱ መጠቀም ነው የምትፈልገው። ወንድሞቻችን እንዲገነዘቡት የምንፈልገው እኛ ጭለማ ውስጥ መኖር አንፈልግም። አምፖል ነው የምንፈልገው። የእኛ ብርሃን ወደ እነርሱ ይጋባ ይሆናል እንጂ አይጎዳቸውም። ከዚህ ይልቅ ኢትዮጵያ ለኢነርጂ የተሻለ እምቅ አቅም ስላላት በዚህ ዙሪያ አብረን ኢንቨስት ብናደርግ፤ በግብርና የተሻለ አቅም ያላቸው ደግሞ በዚያ ዘርፍ ቢያለሙና አብረን ብናድግ የተሻለ ነው። ፍላጎታችን አብረን ማደግ ነው።” በማለትየኢትዮጵያን አቋም ግልጽ አድርገዋል።
የግብጽ እና ሱዳን አዲሱ ፍላጎት ኢትዮጵያ አስገዳጅ ያሉትን ህግ ካልፈረመች በቀጣይ የክረምት ወራት የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በምንም መልኩ እንዳትሞክረው ጫና መፍጠር ነው። ለድርድር የሚያቀርቡትም የውሃ ሙሌቱና ኦፕሬሽኑ በአንድ ላይ እንዲከናወን ነው። በኢትዮጵያ በኩል ሙሌቱና ኦፕሬሽኑ ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች በመሆናቸውን ተቀባይነት እንደማይኖረው ተገልጾላቸዋል። የውሃ አሞላሉንና ኦፕሬሽኑን አንድ ላይ ለመነጋገር የሚያከራክር ጉዳይ ስላለው ጊዜ ስለሚወስድ ውሃ ሳይሞላ ካለፈ ኢትዮጵያ በአንድ ዓመት ብቻ 1 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያሳጣት ተገልጾላቸዋል። ይሁን እንጂ ሁለቱ ሀገራት የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት በያዙት ግትር አቋም ጉዳዩ ከአፍሪካ ህብረት እንዲወጣ ወይም ሌሎች አደራዳሪዎች እንዲጨመሩ ግፊት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ከዚህ አለፍ ካለም ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ለመውሰድ እቅድ ይዘዋል። ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የተጀመረው የሶስትዮሽ ድርድር ገና ባልተቋጨበት ሌሎች አደራዳሪዎችን መጠየቅ የህብረቱን አስተዋፅኦ ማሳነስ ነው።
የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት የሚከናውነው በክረምት የሚዘንበውን ዝናብ በመጠቀም እንጂ ዓመቱን ሙሉ አለመሆኑን ከመጀመሪያው ዙር ሙሌት መገንዘብ ይቻላል። ባለፈው ዓመት በሐምሌ ወር የተካሄደው የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት የዝናብ ውሃ ከፍተኛ በነበረበት ወቅት በመሆኑ ምንም ሳይታወቅ ነበር የተጠናቀቀው። የአሁኑም ከዚህ የተለየ እንደማይሆን ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ በግብጽና ሱዳን በኩል ያለው አዝማሚያ የክረምት ዝናብ ውሃንም ጭምር የሚከለክል ነው። ይህም ዓለም አቀፍ በፍትሀዊነት የመጠቀም መርህን ይቃረናል።
ኢትዮጵያ ለአባይ ወንዝ 86 በመቶ ውሃ የምታበረክት አገር ነች። ነገር ግን 60 በመቶ የሚሆኑ ዜጎችዋ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ባለማግኘት በጨለማ ውስጥ ይኖራሉ። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በጨለማ የሚኖረው ህዝብ የኤሌክትሪክ ብርሃን እንዲያገኝ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም እየገነቡት ያለ ፕሮጄክት ነው። የአባይን ውሃ በፍትሃዊና በእኩልነት መርህ ለልማት ማዋል የኢትዮጵያ ህጋዊና ሉዓላዊ መብት ነው። ስለሆነም የዝናብ ውሃ አትጠቀሙም ለሚሉ ስሞታዎች ቦታ ባለመስጠት በዘንድሮው ክረምት ውሃ የመያዝ ስራ መከናወኑ አይቀሬ ነው። ፕሮጀክቱም የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ልማት የሚያሳድግ እንጂ የውዝግብ ምንጭ አይሆንም።