ቀጥታ፡

ዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛ በትግራይ ክልል ዙሪያ እያስተላለፉት ያለው ዘገባ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ ነው

መጋቢት 21/2013(ኢዜአ) ዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ እያስተላለፉት ያለው ዘገባ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኮሙኒኬሽን አሊያንስ አስታወቀ።

"ሕወሓት" ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ባደረሰው ጥቃት መንግስት በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር እርምጃ መውሰዱ ይታወቃል።

የሕግ ማስከበር እርምጃው መጠናቀቁን ተከትሎ መንግስት "በጥቃቱ እጃቸው አለበት የተባሉ ግለሰቦችን ለሕግ የማቅረብና የሰብአዊ ድጋፍ የማቅረብ" ምዕራፍ በመሸጋገር ለዜጎች ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የኮሙኒኬሽን አሊያንስ በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ባዘጋጀው የዜና ትንታኔ ዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛ በክልሉ ስላለው ሁኔታ እያቀረቡት ያለው ዘገባ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በግልጽ የማያሳይ ነው ብሏል።

የብዙሃን መገናኛዎቹ ሪፖርት "ወገናዊነትና አድሏዊነት" የተሞላበትና ሚዛናዊነት የማይታይበት ነው ሲልም ገልጿል።

መንግስት በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛዎች በትግራይ ክልል ገብተው እንዲሰሩ ፈቃድ መስጠቱን ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን በትግራይ ክልል የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በጋራ ለመመርመር መስማማታቸውንም አውስቷል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የኮሙኒኬሽን አሊያንስ መንግስት በትግራይ ክልል ለዜጎች 70 በመቶ ሰብአዊ ድጋፍ እያቀረበ እንደሚገኝ ቀሪውን በዓለም አቀፍ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች እንደሚሸፈን በትንታኔው ገልጿል።

ይሁንና "የቡድኑ ርዝራዦች" የሰብአዊ ድጋፍ የማስተጓጎልና መሰረተ ልማቶችን የማፍረስ ተግባር እያከናወኑ እንደሚገኝ አመልክቷል።

የፌዴራል መንግስት ወደ ሕግ ማስከበር እርምጃው ከመግባቱ በፊት ከትግራይ ክልል የተወሰኑ የህወሓት አመራሮች ጋር ያለውን አለመግባባት ለመፍታት አስፈላጊውን ጥረት እንዳደረገም በዘገባው ተጠቁሟል።

ይሁንና በአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የደረሰው ጥቃት መንግስት ወደ ሕግ ማስከበር እርምጃው እንዲገባ ምክንያት መሆኑን ገልጿል።

መንግስት በሕግ ማስከበር እርምጃው ንጹሐን ዜጎች እንዳይጎዱና በመሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ጥረት እደተደረገም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የኮሙኒኬሽን አሊያንስ አመልክቷል።

በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎችን ለሕግ የማቅረብ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ፤ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ለሕግ ለማቅረብም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።

በትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት ከአራት ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ እያገኙ መሆኑን ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርም በክልሉ አስተዳደራዊ መዋቅር በመዝርጋት የተቋረጡ አገልግሎቶች ስራ እንዲጀምሩና ዜጎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም