ቀጥታ፡

በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ህገ-ወጥ የዱር እንስሳት አደን መቆጣጠር ተቻለ

ጎንደር መጋቢት 21/2013 (ኢዜአ) በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ህገ-ወጥ የዱር እንስሳት አደን መቆጣጠር በመቻሉ የእንስሳቱ ደህንነት እየተጠበቀ መሆኑን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የህብረተሰብና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ታደሰ ይግዛው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ በሚገኙት ዋልያ ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮዎች ላይ ይፈጸም የነበረውን ህገ-ወጥ አደን ማስቀረት ተችሏል፡፡

የህብረሰቡን የባለቤት ስሜት በማጎልበት ከቱሪዝም ገቢው ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት በመከናወናቸው በዱር እንስሳቱ ላይ ይፈጸም የነበረውን ህገ-ወጥ አደን መቆጣጠር መቻሉን ተናግረዋል።

በፓርኩ ውስጥ ህገ-ወጥ የዱር እንስሳት አደን በመቆሙ በተፈጥሮ ካልሆነ በስተቀር በህገ-ወጥ አደን ጉዳት የሚደርስባቸው ዋልያዎች እንደሌሉ አስረድተዋል፡፡

ቀደም ሲል በፓርኩ ውስጥ የዋልያዎች ቁጥር ተመናምኖ እንደነበር አስታውሰው፤ባለፉት ዓመታት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተከናወነው ጠንከራ ስራ የዋሊያዎች ቁጥር 700 እና የቀይ ቀበሮ ቁጥርም ከ100 በላይ መድረሱን አስታውቀዋል።

የደባርቅ ከተማ የኢኮ ቱሪዝም ህብረት ስራ ዩንየን ስራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ አየነው በበኩላቸው፤ በዩንየኑ አባላት ጥረት የፓርኩን የዱር እንስሳት ህገ-ወጥ አደን ማስቀረት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

ከ8ሺህ በላይ የዩንየኑ አባላት ከቱሪዝም ገቢው ተጠቃሚ ናቸው ያሉት ስራ-አስኪያጁ የአባላቱ ህልውና በፓርኩ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የፓርኩንና የዱር እንስሳቱን ደህንነት በመጠበቅ በኩል ተሳትፏቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1978 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ በአለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው ፓርኩ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡

ፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ ሌሎችም ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፍ መገኛ ስፍራ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም