ቀጥታ፡

ከኢንጂነር ስመኘው ጠንካራ የስራ ባህልን መማር ይቻላል -ባለስልጣናት

አዲስ አበባ  ሀምሌ 22/2010 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ከነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ጠንካራ የሥራ ባህል መማር ይቻላል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ገለፁ። የኢንጂነር ስመኘው ስርዓተ-ቀብር ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተገኙበት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ዛሬ ተፈፅሟል። በወቅቱ ኢዜአ ያነጋገራቸው ከፍተኛ የመንግስት ሹማምንት በሰጡት አስተያየት ኢንጂነር ስመኘው በተለይ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክትን በመምራት ለሰባት ተከታታይ ዓመታት ያሳዩት ትጋት ሁሌም የሚዘከር ምሳሌ ነው። ከግማሽ በላይ ዕድሜያቸውን ህዝብን በማገልገል ያሳለፉት ኢንጂነሩ በዓላማና በቁርጠኝነት ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት የከፈሉት መስዋዕትነት አርአያ የሚሆን ተግባር ነው ብለዋል። በህይወት ዘመናቸው ያሳዩትን መልካም ስራ ለትውልድ በማስተላለፍና የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በውጤታማነት ለማስቀጠል መንቀሳቀስ እንደሚገባም ባለስልጣናቱ አሳስበዋል። በኃላፊነት ላይ የሚገኙ አካላትም ሆኑ ህዝቡ በህይወት ዘመኑ በተተኪው ትውልድ የሚታወስ አገራዊ ታሪክና አሻራ ትቶ ለማለፍ ከኢንጂነር ስመኘው ያለፉት ዓመታት ተግባራት ሊማር ይገባል ብለዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር አሚር አማን እንዳሉት  ''ከእርሳቸው የስራ ባህል በመማር ሁላችንም ሌት ተቀን  ምክንያት ሳንፈጥር እንድንሰራ ፣ሁሌም ለመፍትሄ ጥርሳችንን ነክሰን የምንሮጥ እንድንሆንና የተሻለ አገር ለመገንባትና የለውጥ ሂደቱ እንዳይደናቀፍ ለማድረግ ትልቅ ትምህርት የሰጠ ነው። ስማቸው ከመቃብር በላይ ሆኖ እንዲጠራ ሌት ተቀን መስራት እንዳለብን ከማንኛውም ጊዜ የበለጠ አንድነታችን መጠናከር እንዳለበት ሁላችን ለተሻለች ኢትዮጵያ እንድንሰራ በጽኑ እመኛለሁ።'' የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሙፈሪያት ከሚል በበኩላቸው ኢንጂነር ስመኘው ጀግናና  የልማት አርበኛ ናቸው ፤ ስራቸው ህያው ሆኖ የሚቀጠልና በህዝቡ ልብ ውስጥ ያለ ነው ብለዋል፡፡ “እንዲህ አይነቱን አስቸጋሪ አጋጣሚ ኢትዮጵያውያን እንዴት አድርገን በጥበብ  አንደምንወጣው በእስካሁኑ ሂደት ልምድ አለን እንደህ የሚያስቆጭ አጋጣሚዎች ለበጎ ስሜትና ለበጎ እንቅስቃሴ ጥረት የምናውለው ነው። በእስካሁኑ ልምዳችን ይህን አጠናክረን በተቻለ መጠን አንድነታችን እንዲጎለብትና ሁልጊዜ ሲፈልጉትና ሲጨነቁለት የነበረውን የህዳሴ ግድብ አጠናቆ የሚፈለገውን አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ ልፋታቸውንና ጥረታቸውን ከዳር እንድናደርስ የበኩላችንን ሚና በመጫወት  መሆን ያለበት።'' ነው ያሉት፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዶክተር አብርሀም ተከስተ ''ይዘውት የነበረው ከባድ ሃላፊነት ነው። ከእርሳቸው የምንማረው በጣም ትልቅ ሃላፊነት ነው። በታማኝነት የህዝብን ጥቅም የአገርን ጥቅም ከራስ ጥቅም በላይ ማስቀደምን ትጋትን ጽናትን ነው የምንማረው ለሁላችንም ትልቅ አብነት የሚሆኑ መሪ ናቸው ባለሙያ ብቻ ሳይሆኑ ትልቅ መሪም ናቸው። ከእርሳቸው የህዝብ ፍቅርን እንማራለን።  እንግዲህ የደረሰብን ሀዘን ከባድ ቢሆንም የሳቸውን ራዕይ የእሳቸውን ጥረት ልፋት የምንክሰው የተጀመረውን ፕሮጀክት ከዳር በማድረስ ነው። ሁላችንም ሀዘኑን ወደ ቁጭት ተለውጦ የሳቸውን ስራ ዳር ለማድረስ መነሳሳት በትጋት መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል ሁላችንም ።'' ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓም ነበር በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ያሽከረክሩት በነበረ መኪናቸው ውስጥ በጥይት ተመተው ሞተው መገኘታቸው ይታወሳል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም