ባለፉት 8 ወራት 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚገመት የኮንትሮባንድ እቃ ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት 8 ወራት 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚገመት የኮንትሮባንድ እቃ ተያዘ
ሀዋሳ መጋቢት 21/2013 (ኢዜአ) ባለፉት ስምንት ወራት 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ የወጪና ገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን የፌደራል ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ከሀዋሳና ሞያሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አመራርና ሠራተኞች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ጋር በኮንትሮባንድ ቁጥጥር ዙሪያ በሀዋሳ ተወያይቷል ፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በወቅቱ ለኢዜአ እንደገለጹት ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በመንግስት መዋቅሮች ጭምር በመታገዝ የተደራጀ ሌብነት የሚፈጸምበት የኢኮኖሚ ተግረዳሮት ሆኖ ቆይቷል።
ከለውጡ በኋላ በዘርፉ ያለውን የመከላከልና የቁጥጥር ስራ ስኬታማ ለማድረግ በተደረጉ የአሰራር ማሻሻያዎች ውጤት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
አሰራሮችን ከማሻሻል ጀምሮ አደረጃጀቶችን በማጠናከር ጠንካራ የቁጥጥር ሥራ በመሠራቱ መሠረታዊ ለውጦች መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ስምንት ወራት በተሰሩ የቁጥጥር ሥራዎች 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው የወጪና ገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን ገልዋል።
የተያዙት እቃዎች ግምት ካለፈው ዓመት በ40 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን አመልክተዋል።
በቁጥጥሩ ከተያዙት መካከል አደንዛዥ ዕፅ፣ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ፣ መድሀኒቶች፣ አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስን ጨምሮ ከደረጃ በታች የሆኑና ያልተፈቀዱ ቁሳቁሶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ለቁጥጥር ስራው ውጤታማነት የባለድርሻ አካላት ትብብር አስተዋፅዖ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴው አሁንም በሀገራዊ ለውጡና ኢኮኖሚ ላይ ፈተና መሆኑን ጠቁመው ሁሉም ባለድርሻ አካላት በችግሩ ልክ በመንቀሳቀስ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው ከለውጡ በፊት በነበሩ አመታት የኮንትሮባንድ ንግዱ በተተበተበ የህግ አሰራርና በመንግስት መዋቅሮች በመታገዝ ከፍተኛ የዝርፊያ ሰንሰለት የነበራቸው ሀይሎች መጠቀሚያ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ብልሹ አሰራርን ለማስተካከልና ህገ-ወጥነትን ለመከላከል በተሰራ የማሻሻያ ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማየት እንደተቻለ ጠቁመዋል።
"በዘርፉ ለመጣው ስኬት የመንግስት ቁርጠኝነትና የህዝቡ ትብብር ከፍተኛ ድርሻ አለው" ብለዋል።
በቅርብ ጊዜያት በክልሉ ለተስተዋሉ የሠላም እጦት ችግሮች ኮንትሮባንዲስቶች ዋነኛ የህገ-ወጥ መሳሪያ መጋቢዎች እንደነበሩ ገልፀው ሁኔታውን ለመቀልበስ የክልሉ መንግስት ዋና ዋና የዝውውር መስመሮች ላይ ትኩረት በማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በክልሉ የተዋቀረውን የፀረ ኮንትሮባንድ ግብረ-ኃይል እስከ ታችኛው መዋቀር ድረስ በማጠናከር ትርጉም ያለው የቁጥጥርና መከላከል ሥራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የኮንሶ ዞን ፖሊስ መምሪያ ዋና አዛዥ ምክትል ኮማንደር ሰለሞን ከመይዳ ዞኑ ከፍተኛ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ከሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
በተለይ በአካባቢው የነበረው የፀጥታ ችግር አሁን ላይ መርገብ የቻለ ቢሆንም በግጭቱ ወቅት የነበረው የህገ-ወጥ መሳሪያና ጥይት ግብይት የደራ አንደነበር አስታውሰዋል።
የምዕራብ አርሲ ዞን አባ ገዳ ነጌሶ ገመቹ እንዳሉት በምዕራብ አርሲ አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር መኖሩንና በአርሶ አደሩ ማሳ ጭምር በድብቅ እየተመረተ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ህብረተሰቡ የሁኔታውን አደገኛነት ተገንዝቦ ከመሰል ድርጊት እንዲቆጠብና ወንጀሉን እንዲከላከል በገዳ ስርዓቱ በመታገዝ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ የሀዋሳና የሞያሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ጽህፈት ቤቶቹ በሚሸፍኑባቸው የኦሮሚያ፣ የደቡብ፣ የሶማሌና የሲዳማ አካባቢዎች አመራሮች፣ የፀጥታ አካላት እንዲሁም የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።