ቀጥታ፡

እጅ በመጠምዘዝ ኢትዮጵያን ማንበርከክ አይታሰብም

በገዛኸኝ ደገፉ(ኢዜአ)

የዓለማችን ታዳጊ ሀገራት ከድህነት ለመላቀቅ በሚያደርጉት ትንቅንቅ አንገታቸውን ቀና ማድረግ ሲጀምሩ ምእራባውያኑ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እና በተለያዩ ተንታኞቻቸው በኩል እጃቸውን በማስረዘም የሀገራቱን ግስጋሴ ለመግታት ያለእረፍት መስራት የተለመደ ነው። 

የዛሬ አስር አመት ቱኒዝያዊው የጎዳና ላይ አትክልትና ፍራፍሬ ቸርቻሪ ሞሃመድ ቡአዚዝ ፈቃድ ሳይኖረው ይነግዳል በሚል ምክንያት ከሚሰራበት ቦታ ፖሊሶች ዕቃውን ስለቀሙት አቤቱታውን የሚመልስለት ባለማግኘቱ በመበሳጨትና ተስፋ በመቁረጥ ተወልዶ ባደገባት ከተማ ራሱ ላይ ጋዝ አርከፍክፎ ክብሪት ሲለኩስ ጉዳዩ ትኩረት አግኝቶ የአለም መነጋገሪያ እንደሚሆን የገመተ ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ቡአዚዝ ራሱን ሲያጋይ አጠገቡ የነበሩ ሰዎች ሁነቱን በእጅ ስልካቸው በመቅዳት ወደ ማህበራዊ ሚዲያዎች ካሰራጩት በኋላ በአካባቢው ነዋሪዎች የተቀሰቀሰው የተቃውሞ እንቅስቃሴ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እና የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ቡድኖች ቀንድና ጭራ እየቀጠሉ በከፍተኛ ግነትና ፕሮፖጋንዳ በማጀብ በሰጡት ሽፋን ተቃውሞው ወደ ሁሉም ከተሞች እንዲስፋፋና የፕሬዝዳንት ቤን አሊ ስልጣን እንዲያበቃ ምክንያት ሆኗል።

ይህ ተቃውሞ በምእራባውያን የሚዲያ ተቋማትና በመብት ጥበቃ ቡድኖች አጋፋሪነትና ተንታኞች ብለው በሰየሟቸው ግለሰቦች አራጋቢነት ወደ መካከለኛው ምስራቅ እየተስፋፋ ሲሄድ ምእራባውያን ሀገራት ግጭቱን የሚያረግቡ መፍትሄዎችን ከመሻት ይልቅ እንዲባባስ የሚያደርጉ መግለጫዎችን ከማውጣት ቦዝነው አያውቁም ነበር። በዚህም ምክንያት አመጹ በሊቢያ፣ በግብጽ፣ በሶሪያ፣ እና በየመን ያደረሰው ጉዳት ቀላል የሚባል አይደለም። ይህ ክስተት እነዚህን ሀገራት እስከዛሬ ድረስ ህዝባቸው በማያባራ ጦርነትና ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ እንዲገኙ አድርጓቸዋል። ብዙ ሚሊዮን ዜጎቻቸው ለስደት፣ ለሞትና ለከፋ የአካልና የስነልቦና ጉዳት ከተዳረጉ አስር አመታትን አስቆጥረዋል። 

ምእራባውያን መንግስታት ሉአላዊነታችንን አሳልፈን አንሰጥም የሚሉ ታዳጊ ሀገራትን እጅ ለመጠምዘዝ የሚደግሱላቸው ነገር ቢኖር መፈንቅለ መንግስት ወይም ህዝባዊ አመጽ፣ አሊያም ደግሞ የሃገራት መፍረስና ስርአት አልበኝነት እንዲነግስ ማድረግ ነው። ለዚህም የመንን፣ ሶሪያን እና ቬንዚዌላን መመልከቱ በቂ ነው።

ይህ በሌሎች ሀገራት ላይ የታየው እጅ ጥምዘዛ በትግራይ ክልል የተካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ እና የህዳሴውን ግድብ ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ ለመተግበር ሙከራዎች እየተደረጉ እንዳሉ እየታዘብን ነው።

መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ለፓርላማ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የሚሰሩ አካላትን አስመልክተው “ደሃ ነን ከድህነት ፈጥኖ ለመውጣት ሰላም ያስፈልገናል፤ ድጋፍና ትብብር ያስፈልገናል፤ ነገር ግን ለዚህ ብለን ክብራችንን መሸጥ አይገባንም። እስከነክብራችን ባለንበት እንቀጥላለን እንጂ። ሲመጡ ያመሰግናሉ ያደንቃሉ፤ እዚህ መጥቶ ሳያመሰግን የሄደ የለም። ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ግን ይቀየራሉ። ኢትዮጵያ ከሁሉም ህዝቦች ጋር በሰላም በትብብር በዓለም አቀፍ ህግጋት ራሷን መለወጥ የምትፈልግ ሀገር መሆኗን ማወቅ ከዚያ ባለፈ ግን ማስደንገጥና ማስፈራራት ምንም የማይፈይድ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልል።” በማለት ነበር ማንኛውንም አይነት እጅ ለመጠምዘዝ የሚደረግ ሙከራ እንደማትቀበል የገለጹት።

ሁሉም ለማለት ቢያስቸግርም ጥቂት የማይባሉ በምእራባውያን የሚደራጁ የእርዳታ ድርጅቶች “ህብረተሰቡን ማንቃት” እና “ለሰዎች መብቶች ጥብቅና መቆም” በሚል ሽፋን ድሃ ሃገራት ውስጥ የሚፈጠሩ የህዝብ ጥያቄዎችን ከመጠን በላይ በማጋነንና እንዲባባሱ በማድረግ ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ እንዲሆኑና ህዝብ በመንግስት ላይ ያለውን እምነት እንዲያጣ አቅደው የሚሰሩ አሉ። እነዚህ ድርጅቶች የመንግስትን ሚና ተክተው ሀገር እስከማስተዳደርና የሃገራቱ እጣ ፈንታ ላይ እስከመወሰን የደረሰ ዝንባሌ ያሳያሉ። ለዚህ ተግባር እንዲያመቻቸው የሀገራቱን ከፍተኛ ባለስልጣናት በተለያየ መልኩ የጥቅም ትስስሮች ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ የመንግስትን አስተዳደር በራሳቸው ልክና መልክ ለመቅረጽ ጥረት ያደርጋሉ።

ለዚህም ከህወሃት ጁንታው ቡድን ጋር የቆየ የጥቅም ትስስር የነበራቸው አካላት በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ ህወሃት በሚፈልገው መንገድ እንዲጓዝና የህወሃት ሚና ቀድሞ ከነበረው በላይ እንዲሆን አሊያም ለውጥ እንዳይኖር ለማድረግ በርካታ ጥረቶችን በመገናኛ ብዙሃን፣ በተንታኞቻቸው እና በሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች በኩል ሌት ተቀን ሲሰሩ እንደነበር ማሳያ ነው።

የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት የነበሩት ጂሚ ካርተር፣ ኸርማን ኮህን፣ ጃንዳይ ፍሬዘር፣ ሱሳን ራይዝ እና የመሳሰሉት ለህወሃት ባላቸው “ጥልቅ ፍቅር” የተነሳ ድርጅቱን ያልተገባ ስምና ዝና በመስጠት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲፈጸሙ የነበሩ አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች፣ ዝርፊያ፣ ግድያ እንዲሁም የሰዎች ደብዛ መጥፋት እንዳላዩ ሲያልፉ እንደነበር የአደባባይ ሚስጥር ነው።

ከዚህ ውግንናቸው የተነሳ እነዚሁ ግለሰቦችና ድርጅቶች በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ህወሃት ያደረሰውን ጥቃት ከምንም ካለመቁጠራቸውም በላይ እሱን ተከትሎ የታወጀውን ህግ የማስከበር እና የህልውና ዘመቻ መንግስት የጀመረው ከማስመሰል ጀምሮ የእርምጃውን አስፈላጊነት እስከ ማጣጣል ብሎም የህወሃትን ባለስልጣናት ከህግ ተጠያቂነት ለማዳን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

ህወሃት በክፉ እንዲነሳባቸው እንደማይፈልጉ በተለያዩ ቃለምልልሶቻቸውና በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ ያሳበቁት የቀድሞ ዲፕሎማትና የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ሃላፊ የነበሩት ኸርማን ኮህን የህግ ማስከበር ዘመቻው እንደተጀመረ በትዊተር ገጻቸው ላይ የህግ ማስከበር ዘመቻው የእርስ በርስ ጦርነት እንደሆነና ሕወሓት የተደራጀ ሠራዊት ስላለው የፌዴራል መንግስት ዘመቻውን ባይጀምር ይመረጣል የሚል ይዘት ያለው መልዕክት አስተላልፈው ነበር። ይህ አገላለጽና ንጽጽር ፍጹም ስህተት ስለመሆኑና ምን ያህል ለህወሐት ድጋፍ ለማድረግ የታለመ እንደሆነ ምንም የሚያሻማ አይደለም። ኸርማን ኮህን በዚህ ሳያበቁ “ፕሬዚዳንት ባይደን በትግራይ እየተደረገ ያለው የዘር ማጽዳት ዘመቻ መጨመሩ ያስጨነቃቸው በመሆኑ ጠ/ሚኒስትር አብይ በአሜሪካ ኮንግረስ ሴናተር ኮንስ ዴላዌር በኩል በቅርቡ የሚተላለፍላቸውን መልዕክት በቁም ነገር በመውሰድ ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው” ሲሉም በቅርቡ አሳስበዋል።

ሌላኛዋ አፍቃሬ ህወሃት የሆኑት ጃንዳይ ፍሬዘርም በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ስለደረሰው ጥቃት ምንም ሳይገልጹ “ከመርፈዱ በፊት አሜሪካ በዋነኝነት ውጊያውን ለማስቆም ከአፍሪካ ሀገሮች ጋር መስራት” አለባት በማለት ነበር ያሳሰቡት። ሴትዮዋ ያሳሰባቸው የኢትዮጵያ ጉዳይ ሳይሆን የአሜሪካንን ጥቅም ሲሆን ለዚህም በትግራይ በሚደርገው ጦርነት ምክንያት የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በሶማሊያና በሱዳን ዳርፉር የሚኖረው ተሳትፎ ሊቀንስ ስለሚችል አሸባሪዎች መልሰው በማንሰራራት የአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅምች ላይ አደጋ ይደቅናሉ” በማለት ነበር የገለጹት። ከዚህም ባሻገር አሜሪካ እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር የሚደርሰውን የብድር ድጋፍ ማገድ እንዳለባት ያሳሰቡት ጃንዳይ ፈሬዘር የአፍሪካ መንግስታት ኢትዮጵያን ለማስገደድ በፅናት ከቆሙ የፀጥታው ም/ቤት በጉዳዩ ላይ ተግባብቶ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል ጠቅሰው ኢትዮጵያና የህወሃት ሃይሎች ለድርድር መቀመጥ አለባቸው ሲሉም ገልጸዋል።

በኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን ደጋግመው አዲስ አበባ መመላለሳቸው የሚነገርላቸውና ሌላዋ አፍቃሬ ህወሃት የሆኑት ሱዛን ራይዝ በህወሀት አገዛዝ ወቅት የደረሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና በደል ከምንም ሳይቆጥሩ የጁንታው አመራሮችን ስም በማወደስ ይታወቃሉ። Tough Love: My Story of the Things Worth Fighting For በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሃፍ ላይ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ኬንያና ኢትዮጵያን በሚጎበኙበት ወቅት አልሸባብ ያሰማራው አጥፍቶ ጠፊ ግለሰብ ፕሬዝዳንቱን ለመግደል ያደረገውን ሙከራ የኢትዮጵያ የደህንነት መስሪያ ቤት ሃላፊ የነበሩት ግለሰብ አሸባሪውን በመያዝ መኪናቸው ውስጥ አስገብተው በመቆለፍ እንዳከሸፉት በመግለጽ ለህወሃት ባለስልጣናት ስምና ዝና ግንባታ ተግተው ሰርተዋል። ከስድስት አመታት በፊት ተካሂዶ ኢህአዴግ መቶ በመቶ ያሸነፈበትንና ተቃዋሚዎችና ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ፍትሐዊነት የጎደለው ያለውን ምርጫ ፍትሃዊ፣ ትክክለኛና ተአማኒ ስለመሆኑ በጋዜጠኞች ፊት ምስክርነታቸውን የሰጡት ሱዛን ራይስ በትግራይ ክልል የተደረገው የህግ ማስከበር ዘመቻ ከዘር ማጥፋትና ጭፍጨፋ ጋር አያይዘው ትክክል ያልሆነ ምስል እንዲያዝ በማድረግ በተመድ በኩል በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

በእንደነዚህ አይነት ግለሰቦችና እነሱን እየተከተሉ ለሁኔታው የተለየ መልክ ለመስጠት እየሞከሩ ያሉ መገናኛ ብዙሀንን በመጠቀም ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶችና የምእራባውያን መገናኛ ብዙሃን ከአውሮፓና አሜሪካ አንዳንድ ባለስልጣናት ጋር በመናበብ ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና ለማሳደር እንቅልፍ አጥተው በመስራት ላይ መሆናቸውን በየቀኑ ከሚያወጧቸው ትእዛዝ መሰል ማሳሰቢያዎችና መግለጫዎች መገንዘብ ይቻላል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ ስለዚህ ጉዳይ በሰጡት ማብራሪያ “አንዳንዶች እውነትን ያዛባሉ፤ ትግራይ ክልል ውስጥ ሰላለው ሁኔታ በየቀኑ "ያሳስበናል" በማለት መግለጫ የሚሰጡ አካላት በሰሜን እዝ ላይ ስለተፈጸመው ጥፋት አንድም ቀን ሲያነሱ አይታይም። ሰሜን እዝ ከመጠቃትም በላይ ውርደት ነው የደረሰበት፤ በተኙበት ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል፣ ሴቶች በሳንጃ ተወግተዋል፣ የሰራዊቱ አባላት በየከተማው በመኪና ተጎትተዋል፤ ስለዚህ ጉዳይ እነዚህ አካላት አያነሱም።” በማለት ነበር የኮነኗቸው።

“ትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታ ያሳስበናል፤ ትግራይ ገብተን የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ መንግስት በሩን ክፍት ያድርግ” ሲሉ የነበሩትና ደጋግመው ስራ ላይ መሆናቸውን እየገለጹ የሚገኙት 135 ለጋሽ ድርጅቶች እስካሁን ፋይዳ ያለው ስራ እየሰሩ ባለመሆኑ 70 በመቶው የሰብአዊ ድጋፍ በመንግስት እየተሸፈነ ይገኛል። በዚህም መሠረት በክልሉ ከሚገኙ 4.5 ሚሊዮን እርዳታ ፈላጊ ወገኖች መካከል 3.2 ሚሊዮን ለሚሆኑት መንግስት ድጋፍ ሲያደርግ በእነዚህ ለጋሾች እየተሸፈነ የሚገኘው ለቀሪው 1.3 ሚሊዮን ህዝብ ነው። ይህንን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ “ብዙዎች በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እየወጡ ስለትግራይ ክልል ህዝብ የሰብአዊ እርዳታ ያሳስበናል እያሉ ትዊት ከማድረግ የዘለለ ለህዝቡ ጠብ የሚል ነገር ያቀረበ የለም። አንድም አገር አንድ ኪሎ ስንዴ ወደ ትግራይ ልኮ የተመለሰበት የለም። የትግራይ ህዝብ የትዊተር ኮንሰርን አይበላም ስንዴ ነው የሚበላው። ያልተገደበ አክሰስ እንዲከፈት ጠየቁ፤ ይህም እንዲከፈት ተደረገ። በዚህም ምንም ለውጥ አልታየም። መንግስት ኢንቨስት ያደርጋል ግለሰቦች ግን በትዊተር ላይ ኮንሰርን አለን በማለት ይጨነቃሉ።” ሲሉ ነበር ያብራሩት።

በምእራባውያኑ ዘንድ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ሚዛናዊነት የጎደለው አተያይ ይስተዋላል። እነዚህ አካላት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ስላለው ሁኔታ ቀርቶ በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ እንኳ አተያያቸው የተዛባ ነው። በመከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመው ጥቃት ለምን ወደ ጎን ይተውታል? በማይካድራ ከተማ የተደራጀ የህወሃት ጁንታ ሃይል በዜጎች ላይ ያደረሰው ጭፍጨፋ ለምን አይገልጹትም? የጎንደር እና የባህር ዳር ኤርፖርቶች ላይ በሮኬት ስላደረሰው ጥቃትና ስለደረሰው ጉዳት ለመብት ቆመናል የሚሉ አካላት ስለምን አልተናገሩትም? ከትግራይ ክልል ወጣ ስንል ደግሞ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ስለደረሰው ጭፍጨፋና መፈናቀል ለምን አያነሱም? መልሱ ቀላል ነው ዋነኛው ትኩረታቸው የመንግስትን እጅ ለመጠምዘዝ ስለሆነ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም “ጨኸት ሁሉ አንድ ቦታ የሆነበት ምክንያት የዓይን መንሸዋረር እንጂ የበደል ልክን አያሳይም። አጋጣሚውን በመጠቀም እጅን ለመጠምዘዝ የሚሞክሩ ናቸው። ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው እጅ ለመጠምዘዝ ለተደረጉ ሙከራዎች ተሸንፈው አያውቁም። አሁንም እጅ በመጠምዘዝ የሚሆን ነገር የለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ተላላኪ መንግስት አልነበረም፤ አሁንም አይኖርም። በጋራ ጥቅም ላይ ተከባብሮ አብሮ መኖር ግን ይቻላል።” በማለት ነበር ይህን ሃሳብ ያጠናከሩት።

የሕወሓት ጁንታው ቡድን በምእራቡ ዓለም የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎችን ለሚያቀላጥፉለት ለእነ ማርቲን ፕላውት፣ አሌክስ ዳዋል፣ ፕሮፌሰር ትሮንቮል፣ ሪኔ ሊፍሮና ለመሳሰሉት በርካታ ሚሊየን ዶላሮችን በማፍሰስ የሰሩትን ሃጢያት ለመሸፋፈን እና መልካም ገጽታ ለመላበስ በሚያደርጉት መፍጨርጨር  ከነጮቹ በስተቀር ለትግራይ ህዝብ የሚያስብ መንንግስትም ሆነ ህዝብ የለም የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ይጥራሉ። እነዚህ አፍቃሬ ህወሃቶች ተበደለ የሚሉት ህዝብ በእነሱ ቅስቀሳ ምክንያት ሃገር አልባ ሆኖ ሲፈናቀልና በየስደተኛ ማእከላቱ ሲንከራተት አለፍ ሲልም ውቅያኖስና ባህር ሲበላው እርዳታ መስጠትና ኑሮውን ማረጋጋት ቀርቶ ዘወር ብለው እንደማያዩት የሶማሊያ፣ የየመን እና የሶሪያ ዜጎች ህያው ምስክሮች ናቸው።  

በትግራይ ክልል የተካሄደውን ህግ የማስከበር ዘመቻ ተከትሎ አጋጣሚውን በመጠቀም እጅን ለመጠምዘዝ የሚሞክሩ አካላት የመኖራቸውን ያህል ለጥፋት የተሰለፈ ገንዘቡንና ጊዜውን በደንብ አስልቶ ተደራጅቶ የሚሰራ ኃይል ስለመኖሩም የማይካድ እውነታ ነው። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በብዙ ፈተናዎች ተፈትና ያለፈች፣ በሀገራቸው ጉዳይ የማይደራደሩ ቆራጥ ልጆች ያላት፣ ያልተገባ ጫናን ጥቃትን መድሎን በዘመናት መካከል የተሻገረች ሀገር በመሆኗ ፈጽሞ እንደማትፈርስ መዘንጋት የለበትም። አበቃላት፣ ወደቀች፣ ተበተነች ስትባል የማትወድቅ ሀገር መሆኗን በተደጋጋሚ አሳይታለችና።ቸር እንሰንብት!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም