ቀጥታ፡

የመገናኛ ብዙሀን ግዴለሽ የቋንቋ አጠቃቀም ባህል እንዲበረዝ እያደረገ ነው

ደሴ መጋቢት 20/2013 (ኢዜአ ) በኢትዮጰያ መገናኛ ብዙሃን ግዴለሽ የቋንቋ አጠቃቀም ባህልና እሴት እየተበረዘ በመሆኑ ከወዲሁ ሊታረም እንደሚገባ ምሁራን አሳሰቡ።

"በነባር እሴቶቻችን ኢትዮጵያን እናሻግር" በሚል መሪ ቃል በወሎ ዩንቨርሲቲ ለሁለት ቀናት የተካሄደው 4ኛው ሀገር አቀፍ የቋንቋና ባህል አውደ ጥናት ትናንት ተጠናቋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ልሳን መምህርና ባለሙያ ፕሮፌሰር ጌታሁን አማረ እንደገለጹት መገናኛ ብዙሃን ባላቸው ሀገር የመገንባት አቅም አራተኛው መንግስት እስከመባል ደርሰዋል።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ በሀገራችን መገናኛ ብዙሀን  የሚስተዋለው ግዴለሽ የቋንቋ አጠቃቀም ሀገር ከመገንባት ይልቅ የህዝብ ባህልና እሴት እንዲበረዝና  እንዲናድ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የመገናኛ ብዙሀኑ የግዴለሽነት የቋንቋ አጠቋቀም ሀገሪኛ ቋንቋዎች ጨምሮ ለባህልና እሴቶች መበረዝ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን አመልክተዋል።

በመገናኛ ብዙሀኑ ግንደ መሰረቱ የማይታወቅና  ጉራማይሌ   የቃላት አጠቃቀም  ለሀገራዊ  ቋንቋ ጨምሮ  ለባህልና እሴቶች መበረዝ  ዋና ምክንያት እየሆነ  መምጣቱን  ለአብነት ጠቅሰዋል።

"በተጨማሪም መገናኛ ብዙሀኑ በግድየለሽነት የሚጠቀሟቸው ፀያፍ  ቃላት  ህብረተሰቡን  ወደ ቅራኔ ሲወስዱና ህዝብን ለሁከትና ብጥብጥ   ሲዳርጉ  መመልከት  የተለመደ ተግባር እየሆነ ነው" ብለዋል።

በመንግስት ደረጃም ይሁን በሙያ ማህበራት ደረጃ ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠትና የሚጠይቅ አካል መጥፋቱ ደግሞ ለችግሩ መባባስ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።

በተቋማቱ እየተስተዋለ ያለውን መሰረታዊ የቋንቋ አጠቃቀም ችግር ከወዲሁ ማረምና ማስተካከል ካልተቻለ በቀጣዩ ትውልድ ላይ  አሉታዊ  ጫና የሚያሳድር  መሆኑን  አመላክተዋል።

በመገናኛ ብዙሀኑም ሆነ በሚመለከተው የመንግስትና የሙያ ማህበራት ደረጃ  ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራና እርምት ሊወሰድ  እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

 የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አበረ አዳሙ "የብዙሃን መገናኛዎች ቋንቋ አጠቃቀም" በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ በሀገሪቱ አንጋፋ በሚባሉ መገናኛ ብዙሀን ጭምር ግዴለሽ የቋንቋና የቃላት አጠቃቀም ችግር እንደሚስተዋል ጠቁመዋል።

በተቋማቱ እየተስተዋለ ያለው የቃላት አጠቃቀም ግድፈት  ሀገራዊ ባህልና እሴቶችን የሚበርዝ መሆኑ ደግሞ ችግሩን አሳሳቢ ያደረገው መሆኑን አመልክተዋል።

መገናኛ ብዙሀኑ ለስርጭት እንደሚጠቀሙባቸው የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ሁሉ ችግሩ እንደሚስተዋል የጠቀሱት አቶ አበረ ለአማርኛና ሌሎች ሀገራዊ ቋንቋዎች አቻ ቃል ሳይጠፋ  የእንግሊዘኛ ቃል መጠቀም፣ ቋንቋን መቀላቀል፣ የማይታወቅ ቃል ፈጥሮ መገልገል በስፋት የሚስተዋሉ የቋንቋ አጠቃቀም ግድፈቶች መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

በተጨማሪም የቁጥርና የጾታ ስህተት መፈጸም፣ የአረፍተ ነገር አወቃቀር፣ ሃሳቡን  በማዛባት  አድማጭ፣ አንባቢና ተመልካችን ማወዛገብና ሌሎች  መሰረታዊ  የቋንቋ አጠቃቀም ግደፈቶች በተቋማቱ የሚስተዋሉ መሆኑን ጠቁመዋል ።

በዘርፉ እየታየ ያለውን ችግር  በዘላቂነት ለመቅረፍ የስርዓተ ትምህርት  ማስተካከያ  መደረግ  እንዳለበት ጠቁመው መገናኛ ብዙሃንም ሙያው የሚፈቅደውን የቋንቋ አጠቃቀም መመሪያ መተግበር ፣ ብቃት ያለው ባለሙያ መቅጠርና ሌሎች ተገቢ የሆኑ አሰራሮችን መከተል እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል።

በሀገር ደረጃ የቋንቋ አካዳሚ ወይም ማዕከል ማቋቋምና በባለሙያ የታገዘ ስራ ማከናወን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

"መገናኛ ብዙሃን ጠቀሜታ የሌለው ዘመናዊነትንና  መጤ ባህልን  በትውልዱ  ላይ  እየጫኑ ነው " ያሉት ደግሞ በደብረማርቆስ ዩንቨርሲቲ የፎክሎር መምህርት ዶክተር ድርቧ ደበበ ናቸው።

ተቋማቱ ከችግሩ ለመላቀቅ ቋንቋን፣ ባህልንና እሴቱን ጠንቅቆ የሚያውቅ ባለሙያ መድበው ማሰራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።

"ተቋማቱ ለዘመናት በሚዘልቁ የህትመት ወጤቶች ጭምር የቋንቋ ግድፈት መፈጸማቸው ለታሪክና ትውልድ ትልቅ አደጋ እየሆነ ነው" ያሉት ደግሞ በአርባ ምንጭ  ዩንቨርሲቲ  የቋንቋና ስነ ጹህፍ መምህር ዶክተር ሀይላይ ተስፋዬ ናቸው።

ህትመት ለረጅም ጊዜ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ስለሚያገለግል በተቋማቱ አርትኦት ስራው ጥንቃቄ ሊደረግበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በአውደ ጥናቱ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የዘርፉ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን በዘርፉ 24 ጥናታዊ ጽህፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም