አፍሪካዊያን በስፖርት ስም እየመጣ ያለውን የባህል ተጽእኖ ለመቋቋም መስራት ይገባቸዋል- የዘርፉ ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካዊያን በስፖርት ስም እየመጣ ያለውን የባህል ተጽእኖ ለመቋቋም መስራት ይገባቸዋል- የዘርፉ ባለሙያዎች
አዲስ አበባ መጋቢት 20/2013 (ኢዜአ)አፍሪካዊያን በስፖርት ስም እየመጣ ያለውን የባህል ተጽእኖ ለመቋቋም መስራት እንደሚገባቸው የአፍሪካ የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች ገለጹ።
የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ፣ የዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍና አገር አቀፍ ስፖርት ፌዴሬሽኖች የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት ተካሂዷል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎችና አመራሮች እንዳሉት አፍሪካዊያን በስፖርት ስም እየመጣ ያለውን የባህል ተጽእኖ ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን አለባቸው።
ስፖርት ባደጉት አገሮች መዝናኛ ከመሆኑም በላይ በኢኮኖሚ፣ ቱሪዝምና ሌሎች ዘርፎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘርፍ መሆኑንም አብራርተዋል።
በአንጻሩ አፍሪካዊያን ከዘርፉ መጠቀም ያለባቸውን ያህል ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
ካሜሩናዊቷ የስፖርት ሳይንስ ባለሙያ ሉኮምግ ካንተር እንደሚሉት አፍሪካዊያን የራሳቸው መገለጫ የሆኑ ስፖርቶችን ያላሳድጉት ሌሎች አገሮች ባሳደሩት የባህል ተጽዕኖ ነው።
በመሆኑም አፍሪካዊያን የባህልና እሴቶቻቸው መገለጫ የሆኑትን ስፖርታዊ ጨዋታዎቻቸውን ዜጎቻቸው እንዲወዷቸው ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
የራስን ባህል ለማሳደግ ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋልም ሲሉ ተናግረዋል።
ከኬንያ፤ ኬንያታ ዩኒቨርቲ የመጡት ፖል ዊኒያና እንደሚሉትም አሁን ላይ በአፍሪካዊያን በብዛት የሚዘወሩትና የሚወደዱ ስፖርታዊ ጨዋታዎች ከሌሎች አገሮች የተወሰዱ ናቸው።
በመሆኑም በቀጣይ የራሳቸው የሆኑ ባህላዊ ስፖርታዊ ጨዋታወችን ጭምር በህዝባቸው እንዲዘወተሩና እንዲወደዱ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ መምህርና የኢትዮጵያ አትሌቲከስ ፌደሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር ባዛብህ ወልዴ እንደሚናገሩት የአህጉሪቱ መለያ የተለያዩ ስፖርታዊ ጨዋታዎችን ለሌላው ዓለም በማስተዋወቅ በኩል ብዙ አልተሰራም።
አፍሪካዊያን የሚያስተምሩበት የስፖርት ሥርዓተ ትምህርትም በቅኝ ገዢዎቻቸው ፍላጎት መቃኘት አንዱ ምክንያት ሲሆን የኢኮኖሚ ችግርም ሌላው ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአህጉሪቱ መገናኛ ብዙኃንም ለውጭ ስፖርታዊ ክንውኖች እንጂ፤ለአህጉር በቀል ስፖርት በቂ ሽፋን በመስጠት ረገድ ውስንነት ይስተዋልባቸዋል ብለዋል።
የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ “የዩኒቨርስቲ ስፖርት ዓለምን ለመቀየር” በሚል መሪ ሃሳብ በኮተቤ ሜትሮፓሊታን ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት ነው የተካሄደው።
በጉባኤው ላይ ከአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት የመጡ የስፖርት ፌዴሬሽን አመራሮችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል።