ቀጥታ፡

በደሴ በ80 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ፕላስቲክና ከረጢት ፋብሪካ ተመረቀ

ደሴ፣ መጋቢት 19/2013 (ኢዜአ ) በደሴ ከተማ በ80 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ "ጢጣ ፕላስቲክና ከረጢት" ፋብሪካ ተመረቀ፡፡


የደሴ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃለፊ አቶ አለባቸው ሰይድ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት ደሴና አካባቢውን ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

ለከተማዋ በማምረቻ ዘርፍ 10ኛ የሆነው  የፕላስቲክና የከረጢት ፋብሪካ መመረቁ ባለሃብቶችና ድርጅቶችን ለመሳብ እየተደረገ ያለው ጥረት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል ።

የፋብሪካውን የኤሌክትሪክ ሃይል ጥያቄ ከክልልና ፌደራል መንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር በመፍታት ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ገልጸዋል።

"ፋብሪካው 500 ለሚሆኑ ዜጎች አዲስ የስራ እድል መፍጠር ያስችላል" ያሉት አቶ አለባቸው የአካባቢው ህዝብ ፋብሪካውን እንደራሱ ሃብት በማየት ሊጠብቀውና ሊንከባከበው እንደሚገባ አሳስበዋል።

የፋብሪካው ባለቤት ሐጅ ሙክታር ይማም በበኩላቸው ፋብሪካውን ገንብቶ ለማጠናቀቅ 80 ሚሊዮን ብር ወጭ መደረጉን አስረድተዋል።

ፋብሪካው በቀን 74 ሺህ ከረጢት የማምረት አቅም እንዳለው ጠቁመው "በኤሌክትሪክ ኃይል ማነስ ችግር አሁን ላይ በቀን 17 ሺህ ከረጢት ብቻ ያመርታል" ብለዋል።

እስካሁን ባለው ዝቅተኛ የማምረት አቅም ከ200 በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን  ሐጅ ሙክታር ጠቁመው ምርቱን በመላ የአገሪቱ ክፍል ማሰራጨት በመጀመራቸው የገበያ እጥረት እንዳልገጠማቸው አስረድተዋል።

የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ወጣት ዘሃቡ በቀለ በሰጠችው አስተያየት የቴክኒክና ሙያ ትምህርቷን ብታጠናቅቅም ስራ በማጣቷ ከቤተሰብ ጥገኝነት መላቀቅ አልቻለችም ነበር፡፡

"አሁን ፋብሪካው በአካባቢያችን ተገንብቶ ስራ በመጀመሩ በተፈጠረልኝ  የስራ እድል ከቤተሰብ ጥገኝነት ተላቅቄ የራሴን ህይወት ለመምራት የሚያስችል አቅም ተፈጥሮልኛል" ብላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም