የኢንጂነር ስመኘውን ሞት ምክንያት ፖሊስ አጣርቶ ለፍርድ እንዲያቀርብ የመዲናዋ ነዋሪዎች ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
የኢንጂነር ስመኘውን ሞት ምክንያት ፖሊስ አጣርቶ ለፍርድ እንዲያቀርብ የመዲናዋ ነዋሪዎች ጠየቁ
አዲስ አበባ ሃምሌ 22/2010 ፖሊስ የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞትን ምክንያት አጣርቶ በአፋጣኝ ለፍርድ እንዲያቀርብ ኢዜአ በአስከሬን አሸኘኛት ፕሮግረም ስነ ስርዓት ላይ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ጠየቁ። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ መኪናቸው ውስጥ ሞተው መገኘታቸው የሚታወስ ነው። የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ስርዓተ-ቀብር ዛሬ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተሰቦቻቸው፣ሀዘንተኞችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ተፈጽሟል። ለኢዜአ አስተያታቸውን የሰጡ ሀዘንተኞች እንዳሉት ጥቃት ያደረሱ አካላት ካሉ ፖሊስ በፍጥነት አጣርቶ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ። ከአስተያየት ሰጭዎች መካከል አቶ አብርሃም ደረሰ እንዳሉት የኢንጅነር ስመኘው ሀዘን የመላው ኢትዮጵያ ሀዘን ነው ፤ በሱ ሀዘን ሁላችንም በጣም አዝነናል፤ ለሞቱ ምክንያት የሆኑ ወንጀለኞችን በአስቸኳይ በመለየት ለህግ መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ለአገር ብሎ ብዙ ሲለፋ የቆየውን የኢንጂነር ስመኘው በቀለሞትን ምክንያት ለህዝብ እንዲቀርብልን እንፈልጋለን ያሉት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጭ አቶ ብርሃን ደሱ ናቸው። «ኢንጂነር ስመኘው ማለት የኢትዮጵያ ህዝብ ልጅ ነው።ታማኝ ፣ ጀግና ዛሬ እሱ ቢሞት ሥራው አይሞትም፤ ብዙ ኢንጂነር ስመኘውን የሚተኩ አሉ ፤ልጆቹን ትቶ ይህችን አገር ከድህነት ለማውጣት በበረሃ የሚታትር ፣በኢትዮጵያ በአፍሪካ የማይተካ ሰው ነው ያጣነው ፡፡ዛሬም ነገም ቢሆን እቅዳችንን ታርጌታችንን ሳንመልስ የማንመለስ ነን የኢትዮጵያ ህዝብ ከመንግስት ጎን ቆመን ለህዳሴው ግድብ መሳካት የድርሻችን በመወጣት በስሙ ሀውልት በቦታው እንዲተከልና ታሪክ እንዲዘክረው እፈልጋለሁ»ስትል ገነት አለማየሁ ብላለች። ሊቀ-ትጉሃን ወንዶሰን ተገኝ «ኢንጂነር ስመኘው የኢትዮጵያ ሰማዕት ነው ፤በቤተክርስቲያን ብዙ ሰማዕታት አሉ ሃይማኖታችንን አንቀይርም ማተባችንን አንበጥስም ብለው የተሰዉ እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግረዋል፤ ኢንጂነር ስመኘው ደግሞ የዘመናችን ሰማዕታት ነው። ለአገሩ ብሎ ነው ሰማዕትነትን የተቀበለው ስለዚህ የሞቱ ምክንያት የሆኑትን አጣርቶ ለፍርድ ያቅርብልን ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ህይወታቸው ያለፈው በጥይት ተመተው መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ዘይኑ ጀማል ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ላይ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። የፖሊስ አባላት የኢንጂነር ስመኘውን አሟሟት ለማጣራት ምርመራ እያካሄዱ መሆኑን የገለጹ ሲሆን የምርመራ ውጤቱን በአፋጣኝ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግም መናገራቸው አይዘነጋም።