ቀጥታ፡

የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና አንድነት ለማስፈን ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ እየተሰራ ነው

ደሴ መጋቢት 19/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና አንድነት ለማስፈን የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አስታወቀ።

ማህበሩ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር "በነባር እሴቶቻችን ኢትዮጵያን እናሻግር" በሚል መሪ ሀሳብ  ያተዘጋጀው 4ኛው ሀገር አቀፍ የቋንቋና ባህል አውደ ጥናት  በደሴ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አበረ አዳሙ በአውደ ጥናቱ ላይ እንዳሉት በኢትዮጵያ ያለው የአብሮነት፣ መተሳሰብና የመረዳዳት እሴቶች ሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የሚቀስሙበት ነበር።

"ይሁን እንጂ ባሳለፍነው 30 ዓመት በተዘራ የሴራ ፖለቲካና የሃሰት ትርክት የጥንት ባህሎቻችንና እሴቶቻችን ተሸርሽረው አሁን ላይ እርስ በእርስ የመለያየትና የመጠፋፋት አደጋ ተጋርጦብን ይገኛል" ብለዋል፡፡

ሀገራችን አሁን ከገጠማት ውስብስብ ችግር ተላቃ የህዝቦች አንድነትና ሰላም የሰፈነባት ለማድረግ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የአንዱ ሐይማኖትና ብሔር ለሌላው ጌጥና ውበት እንጂ ስጋት አለመሆኑን ከታሪካችን በማስረዳት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

ማህበሩ መሰል ዓውደ ጥናቶችና ሌሎች የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮችን በመጠቀም የኪነ ጥበብ ሙያዎች ችግሩን አውቀው በመፍትሄው ላይ ያተኮረ  ስራ እንዲያበረክቱ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በሀገራዊ ዋና ዋና ጉዶዮች ላይ በመመስረት ብሄራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የነበረውን እሴት ለመመለስ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ደራሲያን ማህበር ፕሬዝዳንት ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን በበኩላቸው "በኢትዮጵያ በአሰቃቂ ሁኔታ ሰው መግደል፣ ማፈናቀልና ማተራመስ እየተለመደ መምጣቱ አሳዛኝና አስጨናቂ ነው" ብለዋል።

ለስልጣንና ገንዘብ ፍለጋ ህዝቡን እርስ በእርስ ማጫረስ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመው የወደፊቱን በማሰብ ለሀገር ሉኣላዊነትና አንድነት የሚበጅ መፍትሄ ማፈላለግ እንደሚገባ አመላክተዋል።

"ኢትዮጵያ ለህዝቦቿ ብቻ ሳይሆን ከውጭ ለሚመጡ እግዶችም ምቹና የሚወደድ ባህልና እሴት ነበራት" ያሉት ሊቀ ህሩያን በላይ "እየተሸረሸረ የመጣውን ባህልና እሴት ማጎልበት ከሁላችንም ይጠበቃል" ብለዋል፡፡

"አንዱ ከሌላው ያልተጋባ፤ ያልተዋለደና የልተጋመደ ብሄረሰብ የለም" ያሉት ሊቀ ህሩያን "በእኩልነት ተከባብሮ፣ ተደጋግፎና ተደማምጦ በጋራ መኖር ካልተቻለ እጣፈንታችን ተያይዞ መጥፋፋት ነው" ሲሉም አሳሳቢነቱን አመላክተዋል።

የወሎ ዩኒቭርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አፀደ ተፋራ ወጣቱ ትውልድ የአባቶችን ታሪክ በትክክል ተረድቶ የሀገሩን ባህልና ወግ መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የገጠመንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ዩንቨርሲቲው ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት በሀገር በቀል እውቀቶች ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ ፈጠራና ስልጠና በመስጠት ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

"ነባር የአብሮነትና የመተጋገዝ እሴትና ባህሎቻችን መሸርሸር የእርስ በእርስ እልቂትን እያመጣ ነው" ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፎክሎርና የስነ-ጹህፍ መመህር ዶክተር መሃመድ አሊ ናቸው፡፡

ለሁለት ቀን በሚቆየው ዓውደ ጥናት  ከ30 በላይ የጥናት ስራዎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው  ከወጣው መርሃ ግብር ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም