"ብልጽግና በሀገራችን ላይ የተጠነሰሰን የፖለቲካ ሴራ ያስወገደ ህዝባዊ ፓርቲ ነው" - አቶ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
"ብልጽግና በሀገራችን ላይ የተጠነሰሰን የፖለቲካ ሴራ ያስወገደ ህዝባዊ ፓርቲ ነው" - አቶ አገኘሁ ተሻገር
ደብረ ማርቆስ፣ መጋቢት 19/2013( ኢዜአ) "ብልጽግና ባለፉት ዓመታት በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተጠነሰሰን እኩይ የፖለቲካ ሴራ ያስወገደ ህዝባዊ ፓርቲ ነው ሲሉ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ አገኘው ተሻገር ተናገሩ።
ፓርቲውን የሚደግፍ ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ በደብረማርቆስ ከተማ ተካሂዷል።
ሰልፈኞቹ "ኢትዮጵያ በጥፋት ሀይሎች እንዳትፈርስ እንታደጋታለን"፣ "መንገዶች ሁሉ ወደ ብልጽግና ይወስዳሉ"፣ "የኢትዮጵያ ብልጽግናዋ እውን ይሆናል" የሚሉና ሌሎች መፈክሮች በማሰማት ለፓርቲው ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል ።
የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ አገኘሁ ተሻገር በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ብልጽግና በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተጠነሰሰን እኩይ የፖለቲካ ሴራ ያስወገደ ህዝባዊ ፓርቲ ነው።
"ፓርቲው የአማራ ህዝብ ለዘመናት በሃሰት ትርክት ይደርስበት የነበረውን ግፍ ያስቆመ ድርጅት ነው " ሲሉም ተናግረዋል።
ፓርቲው በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ተጭኖ የነበረውን እርስ በእርስ የመጠራጠርና ያለመተማመን ችግር ነቅሎ ለመጣል እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ብልጽግና ፓርቲ በምርጫ አሸንፎ ስልጣን ቢይዝ የኢትዮጵያን አንድነትና የህዝቦችን ደህንነት በማስጠበቅ ወደ ላቀ የልማት ጎዳና ለማራመድ አልሞ እየሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
"የአማራ ህዝብ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች በጥበብ ተቋቁሞ የሚያልፍ፣ አግላይ ያልሆነ፣ ሁሉን የሚያቅፍ፣ በአንድነትና በወንድማማችነት የሚያምን የጽናት ተምሳሌት ነው" ብለዋል።
"ወደፊትም የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጥበብ በማለፍ ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን አንድነታችን ለማጠናከር ህዝቡ በመጪው ምርጫ የብልጽግና ፓርቲን እንዲመርጥ" ሲሉም ጠይቀዋል።
"ብልጽግና ፓርቲ የሀገሪቱን መጻኢ እድገት የሚያፋጥንና የወጣቱን እጣፈንታ የሚያለመልም ነው" ያሉት አቶ አገኘሁ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በደብረ ማርቆስ ከተማ የተካሄደው ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ታላቅ ራዕይ የሚያየውን የአማራን ህዝብ ታላቅነት የሚያንጸባርቅ በመሆኑ ምስጋና አቅርበዋል።
የምስራቅ ጎጃም ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ አብረሃም አያሌው በበኩላቸው ለ27 ዓመታት የህዝቦችን አንድነት ሲሸረሽር የነበረው የህወሀት ጁንታ በተሸኘበት ማግስት የሚካሄደው የዘንድሮ ምርጫ ለሀገሪቱ ህዝቦች አዲስ ተስፋ ይዞ የመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
"ብልጽግና ፓርቲ በሀገሪቱ ላይ ተጋርጦ የነበረውን ጭቆናና መከራ በማስወገድ ወደ ብርሃን ጉዞ የሚያመራ ነው" ብለዋል ።
ፓርቲው አሁን ላይ የህዝቡን ችግሮች እየፈታ ያለና ወደፊትም ለመፍታት የተዘጋጀ መሆኑን አመላክተዋል።
"ብልጽግና በጋራ ሆነን የላቀችና የበለጸገች ኢትዮጵያን የምንገነባበትን አማራጭና እድል ይዞ የመጣ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
" ብልጽግና መምራት ከጀመረ ወዲህ ዞናችን የለውጥ ጭላንጭሎች እያሳየች በመሆኑ ድጋፋችንን ለመግለጽ ሰልፍ ወጥተናል" ያሉት ደግሞ በደብርማርቆስ ከተማ የቀበሌ 02 ነዋሪ ወይዘሮ በላይነሽ ይሄይስ ናቸው።
በድጋፍ ሰልፉ ከደብረማርቆስ ከተማና አካባቢው እንዲሁም ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች፣ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን የጎዛምን ወረዳ ፈረሰኖች ለሰልፉ ድምቀት ሰጥተውታል ።