ቀጥታ፡

በዘንድሮው ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪ.ሜትር ውድድር አትሌት ፋንታዬ በላይነህ አሸነፈች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19/2013 ( ኢዜአ) የዘንድሮውን ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪ.ሜትር የሩጫ ውድድር አትሌት ፋንታዬ በላይነህ በአንደኝነት ስታጠናቅቅ አትሌት መድህን ገብረሥላሴ እና ፈታው ዘርዓይ ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን አጠናቀቁ፡፡

መነሻና መድረሻውን አትላስ መብራት ያደረገው ቅድሚያ ለሴቶች የሩጫ ውድድር የኮሮና ቫይረስ መከላከል ፕሮቶኮልን ጠብቆ ተከናውኗል።

ከውድድሩ በፊት የሙቀት ልኬት መደረጉን እና ለመከላከያ የሚረዱ የፊት ማስክ፣ ሳኒታይዘር እንዲሁም ተሳታፊዎችም ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲወዳደሩ ተደርጓል።

በውድድሩ ላይ የታደሙት የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ እንዳሉት 51 በመቶ የሀገሪቱን ህዝብ ቁጥር የሚሸፍኑ ሴቶችን ማእከል አድርጎ መስራት ካልተቻለ አገራዊ እድገት ሊኖር አይችልም።

እንደዚህ አይነት ዝግጅቶች የሴቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት ትልቅ አቅም እንዳለው ገልጸው ማህበራዊ ግኑኝነታቸውን በማጠናከር ረገድም የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።

ውድድሩ ሴቶች ይበልጥ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶችን ሁለንተናዊ አቅም ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራትን በአስር አመት መሪ እቅድ ውስጥ አካቶ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለዚህም ፖሊሲ ከማዘጋጀት ጀምሮ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ውድድሩን አትሌት ፋንታዬ በላይነህ በ15 ደቂቃ ከ19 ሰከንድ በመግባት ቀዳሚ ስትሆን አትሌት መድህን ገብረሥላሴ እና አትሌት ፈታው ዘርዓይ ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡

የውድድሩ አሸናፊዎች በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚያነሳሳቸው ተናግረዋል።

በውድድሩ ላይ በርካታ ሴት ታዋቂ አርቲስቶች፣ አንጋፋ አትሌቶች እንዲሁም በማህበራዊ ሚድያ ተጽእኖ ፈጣሪ ሴቶች ተሳትፈዋል።

ለ18ኛ ጊዜ ዘንድሮ የተካሄደው ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪ.ሜትር የሩጫ ውድድር "የኢትዮጵያ ሴቶችን ስኬት እናክብር" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተካሄደው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም