ቀጥታ፡

በእስካሁኑ የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር በርካታ ተመልካቾች ወደ ስታዲየም መግባት ስጋት ሆኖ ቆይቷል

መጋቢት 19/2013/ኢዜአ/ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ የአስካሁኑ ውድድር በርካታ ተመልካቾች ወደ ስታዲየም መግባት ለጤና እና ፀጥታ ስጋት ሆኖ መቆየቱን የኢትዮጵያ ፕርሚየርሊግ አክሲዎን ማኅበር ገለፀ።

የኢትዮጵያ ፕርሚየርሊግ አክሲዎን ማኅበር በ16 ሳምንታት በተደረጉ የፕሪሚየርሊግ ጨዋታዎች ዙሪያ ከክለብ ሥራአስኪያጆች ፣ አሰልጣኞችና የቡድን መሪዎች ጋር በመሆን ግምገማ አካሂዷል።

የውድድርና ሥነሥርዓት ኮሚቴው አባል አቶ ዮናስ ገብረማርያም እንዳሉት በራሳቸው ከተማ የሚጫወቱ ቡድኖች ጨዋታቸውን ሲያደርጉ በስታዲየሞች የተመልካች ቁጥር በዝቶ ይታይ ነበር።

በስታዲየሙ ከሚመደቡት ውስን የፀጥታ ሰዎችና ከህክምና ባለሙያዎች ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በየስታዲየሙ በርከት ያሉ ተመልካቾች ይገቡ እነደነበር አስታውሰዋል።

ይህ ደግሞ በውድድር ወቅት ፀጥታን በተገቢው መንገድ ለመቆጣጠርና የኮቪድ ፕሮቶኮሎን ለመጠበቅ ያስቸግራል ብለዋል።

አቶ ዮናስ በመግለጫቸው የተመልካች እና የሙያተኛ መግቢያ ባጆችን በመሸጥና ሐሰተኛ ባጆችን አመሳስሎ በመስራት ተመልካች እንዲገባ ይደረግ እንደነበር አንስተዋል። 

በሌላ ኩል የሥነ ምግባርና ይግባኝ ኮሚቴ ተወካዮች ዘግይቶ መድረስና የክለቦች የቦርድ አባላት ሥራ አስፈፃሚዎች ስም ዝርዝር ቀድሞ አለመዘጋጀት ለአወዳዳሪው አካል ችግር ፈጥሯል ብለዋል።

የዳኝነት እንከኖች፣ ውድድሩን ለሚመሩት አወዳዳሪ አካላት የቀረበው ትራንስፖርት የተቆራረጠ መሆንና የጎል መረብ ጥራት ማነስም አንዱ ችግር መሆኑን አቶ ዮናስ ገልፀዋል።

የክለብ ወጌሻዎችም ቡድናቸው በሚመራበት ወቅት ሰዓት ለማባከን የሚያደርጉት ተግባር እና ተጨዋቾች የዳኛ ውሳኔን ባለመቀበል የሚያደርጉት ከበባም የውድድሩ አሉታዊ ገፅታ ነበር ብለዋል።

በቀጣይ በሚኖሩ ውድድሮች ወደ ስታዲየም ከተፈቀደላቸው ሰዎች ውጪ ተመልካች እንዳይገባ በባጅ የሚገባው በስም ዝርዝር እየታየ እንዲሆን ይደረጋል ብለዋል።

የደጋፊዎች ጥምረት አባላትም የራሳቸው ቡድን ጨዋታ ሲኖር ብቻ እንዲገቡ እንደሚደረግም ገልፀዋል።

የዳኖች ምደባን በተመለከተ ብቃታቸው እንዲፈተሽና የጨዋታ ሪፖርቶችን በቶሎ እንዲያስገቡ በማድረግ ችግሮችን ለመቅረፍ ይሰራል ብለዋል።

የ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር ውድድር በአዲስ አበባ ፣ ባህርዳር እና ጅማ የተካሄደ ሲሆን ቀሪ ጨዋተዎች ደግሞ በድሬድዋና ሐዋሳ ከተማ የሚካሄዱ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም