ቀጥታ፡

የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና ወስደው ወደስራ ተሰማርተዋል - ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

መጋቢት 18/2013 (ኢዜአ) ለአገራዊው ምርጫ ስልጠና የወሰዱ ምርጫ አስፈጻሚዎች ወደስራ መሰማራታቸውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት ስልጠና መስጠት አለመቻሉንም ገልጿል።

ቦርዱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመራጮች ምዝገባ አጀማመር፣ የመራጮች ምዝገባ እንዲሁም የምረጡኝ ቅስቀሳና የአየር ሠዓት ድልድልን በተመለከተ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያይቷል።

ቦርዱ ለ20 መሪ አሰልጣኞች፣ ለ200 ዋና አሰልጣኞችና ለ3 ሺህ 500 የመስክ አሰልጣኞች ስልጠና መስጠቱን ገልጿል።

የመስክ አሰልጣኞቹ በአገሪቷ በተዘጋጀ 610 የስልጠና ማዕከላት ለ100ሺህ የምርጫ አስፈጻሚዎች ሰልጠና መስጠታቸውም ተገልጿል።

ስልጠናውን የወሰዱት በምርጫ ጣቢያ የምርጫ አስፈጻሚዎችም ወደተመደቡባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ተሰማርተው የምርጫ ጣቢያዎችን እየከፈቱና የመራጮች ምዝገባ እየጀመሩ መሆኑም ተነግሯል።

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ስልጠናዎች የተሰጡ ቢሆንም በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ሳቢያ መስጠት እንዳልተቻለ ገልፀዋል።

በኦሮሚያ ክልል በቄለም ወለጋ፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በምስራቅ ወለጋና በሆሮ ጉዱሩ የጸጥታ ችግር በመኖሩ ቦርዱ መረጃ እየጠበቀ መሆኑን ገልፀዋል።

ሰሞኑን በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ባጋጠመው የጸጥታ ችግር በሁለት ምርጫ ጣቢያዎች  ስልጠናው እንዳልተሰጠና የቁሳቁስ ስርጭት እንዳልተከናወነም ተናግረዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞንም በኤፌሶንና ማጀቴ የምርጫ ክልሎች ሥራ መጀመር አልተቻለም ነው ያሉት።

ከተገለጹት ውስን ችግሮች ባሻገር በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችና በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው የመራጮች ምዝገባ መጀመሩን ወይዘሪት ብርቱካን ገልጸዋል።

የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ለማጓጓዝ አጋጥሞ የነበረው የትራንስፖርት ችግር  መፈታቱንም ገልፀዋል።

በውይይቱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ለማድረግ በተመደበላቸው የመገናኛ ብዙሃን የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል ላይ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

ፓርቲዎቹ ድልድሉን አስመልክተው ላነሷቸው ጥያቄዎችም ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።

በተጨማሪም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በኦን ላይን ምርጫ ስለሚያከናውኑበት ሁኔታም በቦርዱ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም