አዲስ ትውልድ ፓርቲ በመጪው ምርጫ ተፎካካሪ ሆኖ እንደሚቀርብ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ ትውልድ ፓርቲ በመጪው ምርጫ ተፎካካሪ ሆኖ እንደሚቀርብ አስታወቀ
አዲስ አበባ ሀምሌ 22/2010 አዲስ ትውልድ ፓርቲ ከሁለት ዓመት በኋላ ለሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። ፓርቲው ሶስተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ አካሂዷል። ጠቅላላ ጉባኤው በዚሁ ወቅት የፓርቲውን የመተዳደሪያ ደንብ በማሻሻል የሥራ አስፈፃሚ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ቁጥርን ቀንሷል። በዚህም መሰረት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን ብዛት ከ17 ወደ 9፤ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ደግሞ ከ41 ወደ 21 ዝቅ እንዲል ወስኗል። ይህንን ተከትሎም ጠቅላላ ጉባኤው የምርጫ ቦርድ ተወካዮች በተገኙበት የፓርቲውን ማዕከላዊ እና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን የመረጠ ሲሆን ፓርቲውን በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የነበሩት አቶ ሰለሞን ታፈሰ ባሉበት እንዲቀጥሉ ተስማምቷል። ከዚህም ሌላ ወይዘሮ ማርታ ካሣ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ አቶ አለማየሁ ደነቀ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፣ አቶ መገርሳ ብሩ የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊ፣ አቶ ጌታቸው መኩሪያ ዋና ፀሃፊ፣ አቶ ዜና ማርቆስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ አባ መምህር ድሪባ ሰቦቃ የፋይናንስ አስተዳደር ኃላፊ እና ወይዘሮ ስምረት ዘሪሁን የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል። ከዚህ ቀደም የፓርቲው ፕሬዚዳንት የነበሩትና በውጭ አገር የሚገኙት አቶ አስፋው ጌታቸው የፓርቲው የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ሆነዋል ሲሆን አቶ ከድር ሮባ ደግሞ የወጭ ግንኙነት ተጠባባቂ ኃላፊ እንዲሆኑ ጠቅላላ ጉባኤው ወስኗል። በመጪው 2012 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ ለመሆን እየሰራ መሆኑን ፓርቲው አስታውቋል። ለምርጫው ሰፊ ዝግጅት ማድረግ እንዲቻልም በክልሎች በኃላፊነት የሚሰሩ ጠንካራ የፓርቲው አባላትን በጠቅላላ ጉባኤው ሰይሟል። በዚህ መሰረት በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ አማራ፣ በሐረሪ እና በአፋር ክልሎች አዳዲስ የፓርቲው ተወካይ ኃላፊዎችን ተሹመዋል። አዲስ ትውልድ ፓርቲ ባካሄደው በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤው በውስጡ ተፈጥረው የነበሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ተስማምቷል። ከዚሁ ጋርም አቶ መገርሳ ብሩን ጨምሮ ከዚህ በፊት በነበረ አለመግባባት ከኃላፊነታቸው ተነስተው የነበሩት አመራሮች ወደ ኃላፊነታቸው አንዲመለሱ ተደርጓል። በጉባኤው ላይ ፓርቲው ከፍተኛ የፋይናንስ ዕጥረት እንዳለበት የተገለፀ ሲሆን የአባላት ወርሀዊ መዋጮ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ለመሰብሰብ አባላቱ ተስማምተዋል። ፓርቲው በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና በሌሎች በሚፈጠሩ መድረኮችና ከህዝብ ጋር በመሆን የአገሪቱን አንድነት ለማስጠበቅ የድርሻውን እንዲወጣ ጠቅላላ ጉበኤው ተስማምቷል። የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ (አርንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ) የፓርቲው መለያ እንዲሆንም በጠቅላላ ጉባኤው ፀድቋል።