በመዲናዋ የተገነቡት ጥልቅ ጉድጓዶች የነዋሪዎችን የውሃ ችግር ያቃልላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የተገነቡት ጥልቅ ጉድጓዶች የነዋሪዎችን የውሃ ችግር ያቃልላሉ
መጋቢት 18/2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ያስገነባቸውን አራት ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ፕሮጀክቶች ዛሬ አስመርቋል።
ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ፕሮጀክቶቹ በሸጎሌ፣ በጊዮን በረኪና፣ በፍራንቺስኮ እና በፖላንድ ኤምባሲ አካባቢዎች ነው የተገነቡት ናቸው።
የባለስልጣኑ የፕሮጀክቶች ቴክኒክ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ደበበ ሙለታ በከተማዋ የውሃ አቅርቦት ፍላጎትና ተደራሽነት መካከል ሰፊ ልዩነት መኖሩን ተናግረዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የውሃ ጎድጓድ ቁፋሮ እየተከናወነ እንደሆነም ገልጸዋል።
ግንባታቸው ተጠናቆ ለምረቃ የበቁት አራት የውሃ ፕሮጀክቶች የኅብረተሰቡን የውሃ ችግር በማቃለል ረገድ ሚናቸው የጎላ እንደሆነም አክለዋል።
አራቱ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች በድምሩ በቀን እስከ 9 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ ማምረት ይችላሉ ብለዋል።
ኢንጂነር ደበበ ከ40 በላይ ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑንም ገልፀዋል።
እስከ መጪው ሰኔ በመዲናዋ በአጠቃላይ 55 ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ፕሮጀክቶች ቁፋሮ ይከናወናል ብለዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎችም የውሃ አቅርቦቱ ከከተማዋ ስፋትና ከኅብረተሰቡ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አድንቀው ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።