ቀጥታ፡

በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የግድቡ ግንባታ እንደማይስተጓጎል የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

አሶሳ ሀምሌ 22/2010 ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት እንደማይስተጓጎል የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደተናገሩት የግድቡ ግንባታ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ሞት ታላቅ ሀዘንና ድንጋጤ ፈጥሮባቸዋል፡፡ ኢንጂነሩ በተለይ ባለፉት ስድስት ዓመታት በጉባ በርሃ ሳይበገሩ ህይወታቸውን ለህዝባቸው እና ለአገራቸው ጥቅም አሳልፈው የሰጡ ናቸው፡፡ ለአገር ታላቅ ባለውለታ በሆኑትንና ወደፊትም ብዙ ሊሰሩ በሚችሉት ኢንጂነር ስመኘው ሞት እጃቸው ያሉ አካላት ካሉ ኢትዮጵያዊ ናቸው ብለው ለማመን እንደሚቸገሩም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ የኢንጂነሩ ሞት የሕዳሴውን ግድብ ገንብቶ ከማጠናቀቅ የሚያስቆም አለመሆኑን የተናገሩት ነዋሪዎች ይልቁንም በቀጣይ ለግድቡ የሚያደርጉትን ድጋፍ ለማጠናከር በቁጭት እንዲነሳሱ ያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በተለያየ መስክ በርካታ ምሁራን ማፍራቷን የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ በኢንጂነር ስመኘው ሞት የህዳሴው ግድብ ሥራ እንደማይቆምና በቀጣይ የሚጠበቅባቸውን እንደሚያደርጉ አመልክተዋል ። ፖሊስ የምርመራውን ውጤት በፍጥነት አጠናቆ ለህዝቡ ይፋ ማድረግ እንዳለበት የገለጹት ነዋሪዎቹ በቀጣይ መሠል ድርጊት እንዳይፈጸም ጠንክሮ መስራት የመንግስትና የህብረተሰቡ ትኩረት መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል። የግድቡ ፕሮጀክት የሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት መሆኑን ነዋሪዎቹ አስታውሰው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝብ በግድቡ ግንባታ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚሆን ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ በገንዘብ፣ በቦንድ ግዥ፣ በጉልበትና  በተለያዩ መንገዶች ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፉት ዓመታት ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ አጠናክሮ ከቀጠለ የግድቡ ግንባታ ለአፍታም ሳይቆም ይጠናቀቃል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም