የመንግስት ሠራተኞች ከመጪው ሚያዝያ ጀምሮ የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ይወስዳሉ - ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት ሠራተኞች ከመጪው ሚያዝያ ጀምሮ የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ይወስዳሉ - ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን
መጋቢት 18/2013 (ኢዜአ) ከመጪው ሚያዝያ 2013 ጀምሮ ለመንግስት ሠራተኞች የብቃት ማረጋገጫ ምዘና እንደሚሰጥ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሚዘጋጀው ምዘናው ብቁና ተወዳዳሪ ሠራተኛ ለማፍራት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር በዛብህ ገብረየስ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወደ መንግስት ተቋማት የሚገቡ ሠራተኞችን ሙያዊ ብቃት ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ምዘናው ለሁሉም የመንግስት ተቋማት እንዲያገለግል የጋራ መስፈርት ወጥቶለት መዘጋጀቱንም ገልፀዋል።
ወደ መንግስት ተቋማት አዲስ ለሚገቡትም ሆነ ለነባር ሠራተኞች የብቃት ምዘናውን ለመስጠት በቂ ዝግጅት እስከሚደረግ ከታሰበው በላይ ጊዜ መውሰዱንም ኮሚሽነር በዛብህ ገልጸዋል።
ይሁንና ስለምዘናው የነበሩ ብዥታዎችን የማጥራትና ምዘናው የሚካሄድበት ቦታና ሁኔታም በመመቻቸቱ ከመጪው ሚያዝያ ጀምሮ ይካሄዳል ነው ያሉት።
በአንዳንድ ተቋማት ሲሰጥ የቆየው የብቃት ምዘና በአዲሱ የምዘና መስፈርት የሚካተት እንደሚሆንና ምዘናውን በግል መስጠት የሚፈልጉ ተቋማትም ከኮሚሽኑ ጋር መዋዋል እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
እንደ ኮሚሽነር በዛብህ ገለጻ በቀጣዮቹ ዓመታት የመንግስት ተቋማት የአሰራርና የአደረጃጀት ክፍተቶች በጥልቀት ይፈተሻሉ።
ተመሳሳይ ስራና ዓላማ ይዘው የሚሰሩ ተቋማት ወደ አንድ የሚመጡበት ሁኔታም ይኖራል።
በተለይም ከምርጫው በኋላ የመንግስት ተቋማትን አወቃቀር ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሲቪል ሰርቪሱን ብቁና ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱ ይታወቃል።