ቀጥታ፡

የዘንድሮው ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ሚዛናዊ ሆኖ እንዲከናወን የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ

መጋቢት 17 ቀን 2013 (ኢዜአ) የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ሚዛናዊ ሆኖ እንዲከናወን የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከፍተኛ መሆኑን የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከብሮድካስት ባለስልጣን ጋር በመተባበር ''በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምና ድልድል መመሪያ'' እንዲሁም ''የመገናኛ ብዙሃንና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የስነ-ምግባርና የአሰራር መመሪያ'' ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

መመሪያው ምርጫን አስመልክቶ በሚከናወን የዜና ዘገባ፣ ሪፖርት ወይም ማንኛውም መረጃ የማተም የማሰራጨትና የማቅረብ ተግባር ላይ የሚሳተፍ ማንኛውም የመገናኛ ብዙሃን ወይም ጋዜጠኛ ላይ ተፈጻሚ ይሆናል ነው የተባለው ።

ለምርጫው ሂደት የተዘጋጀው መመሪያ የመገናኛ ብዙሃን በምርጫ ዘገባ ወቅት በሃላፊነት ሚናቸውን ለመወጣት የሚያግዛቸው መሆኑንም የመድረኩ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎች የምርጫ ዘገባ ሚዲያዎች ሃላፊነት በተሞላበት መልኩ እንዲሆን መመሪያው ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲክ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ንጉሴ ምትኩ “በምርጫ ዘገባ ሂደት የመገናኛ ብዙሃን ሊከተሉ የሚገባቸውን ሂደት ግልጽ ለማድረግ መመሪያው ጠቀሜታው የላቀ ነው” ብለዋል።

ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና እንዲሆን ለህዝብ ትክክለኛ መረጃ በማድረስ ሁሉም ሚዲያዎች ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው መመሪያዎቹ መዘጋጀታው መገናኛ ብዙሃን ምን አይነት ዘገባዎችን መስራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

የመገናኛ ብዙሃን የተለያዩ የኤዲቶሪያል ፖሊሲ ቢኖራቸውም ሁሉም ለአንድ አገር ጥቅም የሚሰሩ በመሆኑ በጋራ ሆኖ ለመስራት መድረኩ መዘጋጀቱ የጎላ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።

የአሻም ቴሌቪዥን የዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ታደሰ ዳኛቸው በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃን በምርጫ ሂደት ከህዝቡ ምን የሚጠበቀውንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጅትን በተመለከተ መረጃ መስጠት እንዳለባቸው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም