ቀጥታ፡

የሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የምርጫ 2013 ቃል ኪዳን ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ  መጋቢት 17/2013 (ኢዜአ) የሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ሕብር ኢትዮጵያ/ የምርጫ 2013 ቃል ኪዳን ይፋ አደረገ።

በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች 280 የምርጫ እጩዎችን ያቀረበው ህብር ኢትዮጵያ የምርጫ 2013 ቃል ኪዳን ሰነዱን ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ አድርጓል።

የሕብር ኢትዮጵያ ሊቀ መንበር አቶ ግርማ በቀለ እንዳሉት ብሔራዊ መግባባትና አገራዊ እርቅ የፖለቲካ ፕሮግራማቸው አንዱ አካል ነው።

በኢትዮጵያ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ብሔራዊ መግባባትና አገራዊ እርቅ ሳይደረግ ችግሮችን መሻገርና ዴሞክራሲን ማጎልበትና ሰላምን ማስፈን እንደማይቻል ፓርቲው ያምናል።

የሕብር ኢትዮጵያ የምርጫ ግብረ ሃይል ጽህፈት ቤት አስተባባሪ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው አለመተማመን የኢትዮጵያን ህልውና እየተፈታተነ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ሕብር ኢትዮጵያ በምርጫ አሸንፎ የመንግስትን መንበረ ስልጣን ሲቆጣጠር ከውስጥ ጥንካሬ በመነሳት በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ የውጭ ግንኙነት መርህ ይኖረናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ እንዳንጠቀም ግብፅ የምታሳድረው ተፅዕኖ የሱዳን ሉዓላዊነት መዳፈር እንዲሁም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች የውስጣዊ አለመግባባቶች መንስኤ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የሕብር ኢትዮጵያ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ አበራ በቀለ ፓርቲው ቢመረጥ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።

የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የዋጋ ግሽበትን ባገናዘበ ጥናት ላይ ተመስርቶ የደመወዝ ጭማሪና የገቢ ግብር ቅነሳና የቫት ማስተካከያ ያደርጋል ብለዋል።

በአገሪቱ የነፃ ገበያ ስርዓት የመንግስት ጣልቃ ገብነት ከቁጥጥርና ስርዓት ማስያዝ ያለፈ እንዳይሆን ከማድረግም በተጨማሪ ፖለቲካዊ አንድምታ ብቻ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲ የንግድ ድርጅቶች ከማንኛውም የንግድ እንቅስቃሴ እንዲወጡ ያደርጋል ብለዋል።

በምርጫ የሚወዳደሩ እጩዎችን ለማስመዝገብ በአንዳንድ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ አባሎቻቸው እንግልት ስለደረሰባቸው ዕጩ አለማስመዝገባቸውንም ይፋ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም