ኢዜአ ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ጋር ለመስራት ስምምነት ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ጋር ለመስራት ስምምነት ተፈራረመ
አዲስ አበባ መጋቢት 17/2013 (ኢዜአ )የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ።
የመግባቢያ ሰነድ ስምምነቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ እና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና ተፈራርሟል።
በዚሁ ወቅት ኢንጅነር ወርቁ እንዳሉት ሚዲያዎች አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን መጠቀም ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ መረጃ ለማድረስ ያስችላቸዋል።
ሚድያዎች አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም የተቀላጠፈ መረጃ ለህብረተሰቡ ከማድረስ በተጨማሪ ሌሎች ተቋማት ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የሚሰጡትን አገልግሎት ቀልጣፋ እንዲያደርጉ ማስተዋወቅ ሂደት ላይ ማገዝ ይኖርባቸዋልም ነው ያሉት።
በተለይ በአቅም ግንባታ በርካታ ስራዎችን ከሚዲያ ጋር እንሰራለንም ብለዋል።
በዚህም የሚዲያን ስራ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በመደገፍ ወቅታዊ የሆነ መረጃ ለህዝቡ ለማሰራጨት ትልቅ እገዛ አለው ብለዋል።
ማዕከሉ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም የጥናት፣ የምርምርና የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አብራርተዋል።
ሌሎች አገራት በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ በርካታ ስራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ ከተጀመረ አጭር ጊዜ ቢሆነውም ጥሩ ውጤት እየታየበት መሆኑን ገልጸዋል።
ማዕከሉ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ተቋማት የራሳቸውን ምርት የሚያሳድጉበት፤አገልግሎታቸውን በቀላሉ ወደ ማህበረሰቡ ለማድረስ እንዲችሉ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው ኢዜአ እንደ አገር እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ጋር በጋራ መስራቱ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢዜአ በአገር ውሰጥ ካሉት 18 የሚዲያ ተቋማትን ጨምሮ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጋር እየሰራ ይገኛል ይህም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ከታገዘ የበለጠ ውጤታማ ይሆናል ብለዋል።
በኢኮኖሚ ያደጉ አገራት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በመታገዝ በርካታ ተግባራትን እየከወኑ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማለት ማሽኖች ሰው ሰራሽ የሆነ የማሰብ ክህሎትን በመጠቀም የሰው ልጅን በማገዝ በተለያዩ የሰራ መስኮች እንዲሰማሩ፣ የሰው ስራን ሙሉ በሙሉ በመተካት ራሳቸውን ችለው በፍጥነት ስራ እንዲያከናውኑ፣ የሰው ልጅን የአዕምሮ ችሎታ የሚያስመስል የምህንድስና የሳይንስ እምርታ መሆኑ ይታወቃል።