ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ባማከለ መልኩ ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችል መስራት ይገባል- የምጣኔ ሐብት ምሁራን

 አዲስ አበባ  ደብረ ማርቆስ መጋቢት 17/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ባማከለ መልኩ ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችል መስራት እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ገለጹ።

ኢትዮጵያ ባለፈው በጀት ዓመት የገጠሟትን የተለያዩ ተግዳሮቶች ተቋቁማ ከ6 ነጥብ 1 በመቶ በላይ እድገት ማስመዝገቧን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መግለፃቸው ይታወሳል።
እድገቱ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ባማከለ መልኩ ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችል መስራት እንደሚገባ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ተናግረዋል።

መንግስት በዋናነት ግብርናውን በመደገፍ፣ ኢንዱስትሪን በማስፋፋትና የስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት በማድርግ እድገቱን ፍትሐዊ ለማድረግ መስራት አለበት ብለዋል።


የኢኮኖሚና የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ሁሴን አሊ እንደሚሉት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አገሪቷ  አገልግሎት መስክ እድገት ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል።


የኢኮኖሚ እድገቱ ግን በተለይ በዝቅተኛው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ ውጤት እንዲኖረው ማድረግ ላይ ችግር መኖሩን አብራርተዋል።


ከ
80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአገሪቱ ዜጎች የሚሳተፉበት የግብርና መስክ አለማደግ ሁሉም በፍትሐዊነት ከተገኘው የኢኮኖሚ እድገት ተቋዳሽ እንዳይሆኑ ማድረጉን ገልፀዋል።


በመሆኑም መንግስት ፖሊሲዎቹን በማስተካከልና ብዙሃኑ የማህበረሰብ ክፍል የሚሳተፍበትን መስክ በመደገፍ ሁሉንም ያማከለ ተጠቃሚነት እንዲኖር መስራት ይግባል ብልዋል።

የኢኮኖሚ ተመራማሪው ደረጄ ደጀኔ፤ በአንድ ሃገር የኢኮኖሚ እድገት አለ ተብሎ ሊገለጽ የሚችለው ከግብርና፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከአገልግሎትና ከማእድን ዘርፍ የሚገኝው አመታዊ አጠቃላይ የምርት መጠን ተደምሮ መሆኑን አብራርተዋል።

ሆኖም በአብዛኛው በኢትዮጵያ ውስጥ እድገት እየተመዘገበበ ያለው ጥቂት ሰዎችን ተሳታፊ በሚያደርገው የአገልግሎት ዘርፍ በመሆኑ ፍትሐዊነት ላይ ጥያቄ እያስነሳ መሆኑን ይገልፃሉ ።

መንግስት በተለይ የግብርናውን ዘርፍ በመደገፍና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ አትኩሮ መስራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት በአብዛኛው የሚያዘነብለው በአገልግሎት መስኩ ላይ በመሆኑ የዜጎች የሚታይና የሚጨበጥ አይደለም ብለዋል።

በሀገሪቱ የተመዘገበው እድገት አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል በሚሳተፍበት መስክ ባለመሆኑም በርካታ ዜጎች በዋጋ ግሽበትና በኑሮ ውድነት እየተቸገሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም መንግስት ይሕንን ችግር ሊቀርፍበት የሚያስችለውን ፖለቲካል ኢኮኖሚን በመቀየስ አካሔዱን ማስተካከል ይኖርብታል ብለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሀገሪቱ  ጥቅል ዓመታዊ ምርት 100 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም