የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የኢንጂነር ስመኘው በቀለን ልጆች በትምህርትና በኢኮሚ ለማገዝ ወሰነ። - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የኢንጂነር ስመኘው በቀለን ልጆች በትምህርትና በኢኮሚ ለማገዝ ወሰነ።
መቀሌ ሀምሌ 22/11/2010 የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የልማት ጀግና በሆኑት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማውን ሃዘን ገለፀ። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በሀዘን መግለጫው ላይ እንዳስታወቁት ኢንጅነር ስመኘው የከፍተኛ ሙያ ባለቤት ብቻ ሳይሆኑ ለኢትዮጵያ ህዝብ ልማትና እድገት የተፈጠሩ ሰው ናቸው። በኢትዮጵያ ህዝቦች ጽኑ ፍላጎትና የተባበረ ክንድ የተጀመረውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በማፋጠን የሚታወቁ ከመሆኑም በላይ የብሔር ቢሔረሰቦች ክብር ሆነው ለዘላለም የሚኖሩ ታላቅ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ገልፀዋል። "የትግራይ ክልል መንግስትም የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ልጆች በሚፈልጉት የትምህርት ደረጃ ላይ ለማድረስና አስፈላጊውን ወጪያቸውን ለመሸፈንም ወስኗል" ብለዋል ዶክተር ደብረጽዮን። ከኢንጂነር ስመኘው ጋር ለሰባት ዓመታት ያህል አብረው እንደሰሩ የገለጹት ደክተር ደብረጽዮን ለኢንጂነሩ ልጆች በመንግስት ብቻ ሳይሆን በግላቸውም አስፈላጊውን ክትትል ለማድረግና ድጋፍ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግሯል። ለጀግኖች አክብሮት የሚገለፀው በሀዘን ብቻ ሳይሆን የተነሱበትን ዓላማ ከግብ በማድረስ ጭምር መሆኑ የተናገሩት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ "የሕዳሴው ግድብ ለደቂቃም እንዳይቆም እንሰራለን" ብለዋል። በኢንጂነር ስመኘው ሞት የክልሉ መንግስትና ህዝብ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸው ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለመላ የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናት ተመኝተዋል።