ቀጥታ፡

የሴቶች 5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር የፊታችን እሁድ ይካሄዳል

መጋቢት 17/2013 (ኢዜአ) በየዓመቱ የሚካሄደው ቅድሚያ ለሴቶች 5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር የፊታችን እሁድ ይካሄዳል።

ውድድሩ በሴቶች ዙሪያ የተለያዩ ማህበራዊ መልዕክቶችን ይዞ የሚከናወን መሆኑ ይታወቃል ።

ከነገ በስቲያ እሁድ የሚካሄደውን የ5 ኪሎ ሜትር ሩጫ በማስመልከት የውድድሩ አዘጋጅ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የስትራቴጂክ እና ኢኖቬሽን ኃላፊ ወይዘሮ ዳግማዊት አማረ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ውድድሩ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ 2 ሺህ ዝቅ መደረጉን ገልፀዋል፡

በውድድሩ ላይ 150 አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን በአንደኝነት ለሚያጠናቅቅ የ50 ሺህ ብር ሽልማት መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡

ውድድሩ ሲካሄድ የኮቪድ -19 ፕሮቶኮል ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል።

ተወዳዳሪዎች በሩጫው መነሻና መድረሻ ላይ የፊት ጭምብል የማድረግ ግዴታ አለባቸው ያሉት ወይዘሮ ዳግማዊት የሰውነት ሙቀት ልኬት ይከናወናልም ብለዋል።

ውድድሩ በተቻለ መጠን አካላዊ ርቀትን የጠበቀ እንዲሆን አስፋልት ላይ መስመሮች እንዲኖሩ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶችና ህፃናት እና ወጣቶች ቢሮ የስርአተ ፆታ ቡድን መሪ ወይዘሮ በረከት በቀለ ውድድሩ ሴቶችን ጤናማና ደስተኛ ከማድረጉ ባለፈ ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብን ለመፍጠር ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡

ዘንድሮ ለ18ኛ ጊዜ የሚካሄደው ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር መነሻ እና መድረሻውን አትላስ በማድረግ "የኢትዮጵያ ሴቶችን ስኬት እናክብር" በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም