ቀጥታ፡

የግብይት ሰርዓቱ ቀልጣፋና ዘመናዊ እንዲሆን የባንኮች አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል አለበት ተባለ

መጋቢት 17/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብይት ሰርዓት ቀልጣፋና ዘመናዊ እንዲሆን የባንኮች አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል እንዳለበት ተገለጸ፡፡

ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን እውቅና አግኝተው በክፍያ ፈጻሚነት በመሳተፍ ላይ ከሚገኙ ተቋማት፣ ባንኮችና የስራ ኃላፊዎች ጋር የጋራ የምክክር መድረክ ተከናውኗል ።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢኒንጂነር ኢሌሮ ኡፒየው በዚህ ወቅትእንደገለጹት፤ የምርት ገበያ የግብይት ስርዓት ቀልጣፋና ዘመናዊ እንዲሆን በባንኮች በኩል ያለው የአገልግሎቱ አሰጣጥ ይበልጥ ቀልጣፋ መሆን አለበት።

ተቋማቱም የግብይት ክፍያንና የርክክብ ስራውን በሚፈለገው ደረጃ ማሳካታቸውን በተመለከተ አፈጻጸማቸውን በመገምገም የተሻለ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባም ተናግረዋል።  

በዚህም ሕግን፤ ደንብንና መመሪያን የተከተለ፣ ስነ ምግባርን የጠበቀና ተገልጋይን የሚያረካ አገልግሎት  ለመስጠት እንዲቻል ባንኮች አገልግሎታቸውን ማዘመን አለባቸው ብለዋል።

በመሆኑም ክፍያ የሚፈጽሙ ባንኮች በተለይም ለምርት ገበያው አባላትና ቀጥታ ተጠቃሚዎች በሚቀርባቸው አካባቢ በቴክኖሎጂ  የተደገፈ፣ ጥራትና ቅልጥፍና የታከለበት አገልግሎት በመስጠት በኩል ሚናቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

በባንኮች የተዋቀሩ የክፍያ ቡድኖች አቋም፤አደረጃጃትና አሰራር ፤የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲስተካከል የክፍያ ቡድን አባላት ያላቸውን የአቅም ውስንነት የሚያሳድጉበት ሁኔታ መፍጠር  ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

ከምርት ገበያው ጋር የሚደረገው የኤሌክትሪክ  የክፍያ ትእዛዝ  መረጃ ልውውጥ የበለጠ ቀልጣፋና  ደሕንነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን ከባንኮች ጋር በኮር ባንኪንግ እንዲተሳሰር መደረጉ ደንበኞችን በአግባቡ ለማስተናገድ ይረዳል ብለዋል፡፡

የክፍያ መፈጸሚያ ባንኮች የአገልግሎት አሰጣጥ የሚሻሻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር መስራት ይገባልም ተብሏል፡፡

በምርት ገበያው  አባላትና በደንበኞች ሂሳብ አካውንት አያያዝና የክፍያ ትእዛዝ ልውውጥ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችና መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ተቋማቱ በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የግብይት ስርዓቱ በዚህ አሰራር ውስጥ ማለፉ ለአገር ኢኮኖሚና ለባንኮች ትልቅ ጠቃሜታ እንደሚሰጥ የክፍያ ፈጻሚ ተቋማት ተወካዮች ተናግረዋል ።

በመሆኑም አገልግሎቱን የሚጠቀሙ ባንኮች ደንበኞቻቸውን በስራቸው ለማስደሰት ጠንክረው መስራት አለባቸው ብለዋል።

የግብይቱንና የክፍያ ርክክብ ስርዓቱን ለማሳለጥ እውቅና የተሰጣቸው 17 የክፍያ መፈጸሚያ ባንኮች በስራ ላይ መሆናቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም