"የኢትዮጵያ ፊልም ትዝታዎች እና ቅኝት" በሚል የፊልም ጉባዔ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
"የኢትዮጵያ ፊልም ትዝታዎች እና ቅኝት" በሚል የፊልም ጉባዔ ሊካሄድ ነው
መጋቢት 17/2013/ኢዜአ/ "የኢትዮጵያ ፊልም ትዝታዎችና ቅኝት" በሚል የፊልም ጉባዔ ይካሄዳል ሲል የሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ገለፀ።
የሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ምክትል የቢሮ ኃላፊ አቶ ኤልያስ መንግሥቱ እንደገለፁት በጉባዔው በኢትዮጵያ ሲኒማ ታሪክ ቀዳሚ የሚባሉ ፊልሞች ለዕይታ ይቀርባሉ።
የኢትዮጵያን የፊልም እንቅስቃሴ የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሑፎች ይቀርባሉ፤ በሚቀርቡት ፊልሞች ላይም ከተመልካቾች ጋር ውይይት ይካሄዳል።
በውይይቱ በኢትዮጵያ ፊልም ተግባራዊ ሊደረጉ ይገባል ተብለው የሚታሰቡ ጉዳዮች እንደሚነሱ አቶ ኤልያስ ተናግረዋል።
"የኢትዮጵያ ሲኒማ ሲጀመር አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ አገዛዝ አልወጡም ነበር" ያሉት አቶ ኤልያስ ጉባዔው እንደ አጀማመሩ ያላደገው ሲኒማ ትኩረት እንዲያገኝና እንዲነቃቃ ያደርገዋል ብለዋል።
የፊልም ጉባዔው ከአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ እና ከኩራት ፒክቸርስ ጋር በትብብር ተዘጋጅቷል።
በከተማዋ የሚገኙ የፊልም ትምህርት ቤቶችም ይሳተፉበታል።
በፊልም ጉባዔው ሂሩት አባቷ ማነው፣ አስቴር፣ ጉማ እና በሕይወት ዙሪያ የተሰኙት አራት ሲኒማዎች ለዕይታ እንደሚቀርቡ አቶ ኤልያስ አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ፊልም በ1957 ዓ.ም የተሰራው "ሂሩት አባቷ ማነው?" የሚለው እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ።