ባህርዳር ከተማ ፕሪሚየር ሊጉን ተቀላቀለ

አዲስ አበባ ሀምሌ 22/2010 የባህርዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ ፕሪሚየር ሊጉን ተቀላቀለ። ባህርዳር ከነማ ሶስት ቀሪ ጨዋታ እያለው በ2011 ዓ.ም ፕሪሚየር ሊጉን መቀላቀሉን አረጋግጧል። በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በ27ኛ ሳምንት ኢትዮጵያ መድንን 2 ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ነው ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማለፉን ያረጋገጠው። ዛሬ ከረፋዱ አራት ሰዓት በመድን ሜዳ በተደረገ ጨዋታ ግርማ ደብሳና ሙሉቀን ታሪኩ ባስቆጠሯቸው ግቦች ነው ያሸነፈው። በ27 ጨዋታዎችም 61 ነጥቦችን መሰብሰብ ችሏል። ሶስት ቡድኖች ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚያልፉ ሲሆን ሁለቱ የምድቦቻቸው በበላይነት ከሚያጠናቅቁት አንዱ ቡድን ደግሞ በየምድቦቹ ሁለተኛ የሆኑት በጥሎ ማለፍ አሸናፊ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ይገባል። በምድብ ሀ ሽረ እንደስዓሴ በ26 ጨዋታ 48 ነጥብ በመያዝ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በምድብ ለ ደግሞ 25 ጨዋታ አድርገው ደቡብ ፖሊስ በ48 ነጥብ ሲመራ ጅማ አባቡና በ47 ነጥብ ይከተላል። የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በሁለት ምድብ 32 ክለቦችን እያሳተፈ ይገኛል። ባህርዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ በ1973 ዓ.ም ነው የተመሰረተው።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም