ቀጥታ፡

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ግብፅና ሱዳን የኢትዮጵያን የጋራ ተጠቃሚነትና የመልማት ፍላጎት በውል ሊገነዘቡ ይገባል

መጋቢት 17/2013/ኢዜአ/ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ግብፅና ሱዳን የኢትዮጵያን የጋራ ተጠቃሚነትና የመልማት ፍላጎት በውል ሊገነዘቡ እንደሚገባ የመሬትና ውሃ ሃብት ተመራማሪዎች ገለፁ።

አገራቱ የኢትዮጵያን በጋራ የመልማት እቅድ በውል ተገንዝበው መደገፍ ሲገባቸው በተቃራኒው መቆማቸው ተገቢ አለመሆኑንም ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ ሰሞኑን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ብዙ ፈታኝ ነገሮች ቢኖሩም ግንባታውን እናሳካዋለን ማለታቸው ይታወሳል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መንግስት ለኢትዮጵያ ህዝብ ቃል በገባው መሰረት ተግባራዊ እንደሚያደርገውም አረጋግጠዋል።

የግድቡ ውሃ የመሙላት ሂደት የታችኛው የተፋሰስ አገራት በማይጎዱበት መልኩ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሞላሉን በተመለከተ ከአገሪቱ ጋር በማንኛውም ጊዜ ስምምነት ለመፈረም ኢትዮጵያ ዝግጁ ነች ብለዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የመሬትና ውሃ ሃብት ተመራማሪዎች እንደሚሉት የተፋሰሱ አገራት ዘለቄታዊ የሆነ የውሃ ተደራሽነት ሊኖራቸው የሚችለው የኢትዮጵያ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመሬትና ውሃ ሃብት ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ጠና አላምረው ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የያዘችው አቋም የፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንጂ ማንንም የመጉዳት እንዳልሆነ ይገልፃሉ።

ኢትዮጵያ የተፋሰሱን አገራት ሳትጎዳ የዝናቡን መጠን ባገናዘበ መልኩ ግድቡን የመሙላት ፍላጎቷ በራሱ የትኛውንም አገር የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላትና በሃላፊነት ስሜት እንደምትሰራ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የግድቡ መገንባት አገሪቱ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ኖሯት ኢንዱስትሪዎችን እንድታስፋፋና ለሌሎች አገሮችም የሚጠቅም መሆኑን አንስተዋል።

በአለም አቀፍ የውሃ አስተዳደር ኢንስቲትዩት የውሃና መሬት ነክ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አማረ ሃይለስላሴ እንደሚሉትም የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዓላማው ግልፅ ነው።

በኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር ምክንያት በርካታ ህዝብ በጨለማ እየኖረና ከጭስ ጋር እየተጋለ ህይወቱን እየመራ መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም የግድቡ መገንባት የፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ልማት እንጂ የትኛውንም አገር የማይጎዳ መሆኑን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የምትሻ መሆኑን አንስተው ለተፋሰሱ አገራት ዘላቂ የሆነ የውሃ ተደራሽነት የሚኖረውም በፍትሃዊ አሰራር ብቻ መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም የግድቡን ግንባታና የውሃ አሞላል በሚመለከት ኢትዮጵያ በያዘችው እቅድ መሰረት መቀጠል የኖርባታል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ እንዳትለማና እንዳትጠቀም በማሰብ ግብፅና ሱዳን የግድቡን ግንባታና ውሃ ሙሌት እንዲስተጓጎል እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሁለቱን አገሮች እኩይ አላማ ለማክሸፍም በሁሉም ዘርፍ ላይ የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ዲፕሎማት በመሆን በተለይ በዲፕሎማሲው ላይ የተጠናከረ ስራ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም