ቀጥታ፡

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ሰላም የሚደግፉ ሰልፎች በሽሬ እንዳስላሴና በሑመራ ከተሞች ተካሄዱ

ሽሬ እንዳስላሴ/ሁመራ ሀምሌ 22/2010 በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝቦች መካከል የተፈጠረው ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው በቁርጠኝነት እንደሚቀሳቀሱ የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ። የሑመራ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው ከኤርትራውያን ወንድሞቻቸው ጋር የተፈጠረውን ሰላም በዘለቄታ ማጠናከር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ነዋሪዎቹ ቁርጠኝነታቸው የገለጹት ዛሬ በከተማዋ ባካሄዱት ታላቅ ህዝባዊ የድጋፍ  ሰልፍ ላይ ነው። በሰልፉ ላይ የተሳተፉት ነዋሪዎቹ እንዳሉት በሁለቱ አገራት መካከል የተጀመረው የሰላም፣ የፍቅርና የአብሮነት ጥረት ከዳር እንዲደርስ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው። የከተማዋ ነዋሪና የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት አቶ ይህደጎ ገብረኢየሱስ በሰልፉ ላይ እንዳሉት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ከ20 ዓመታት በላይ የዘለቀው ቅራኔ ተወግዶ በምትኩ የሰላም ብርሃን በመፈንጠቁ ደስተኛ ናቸው። ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደሰላም መምጣታቸው ወንድማማች ህዝቦች ወደ ቀድሞ ፍቅራቸው እንዲመለሱ ስለሚያደርግ የሁለቱ አገራት መንግስታት የወሰዷቸውን እርምጃዎች እንደሚደግፉ ገልጸው፣ ለሰላሙ መጠናከር ጠንክረው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። "በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተጀመረው የሰላም ግንኙነት ዘላቂነት እንዲኖረው ከእኔ የሚጠበቀውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ ነኝ” ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ዘነበች በላይ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው። ወጣት በላይ መብርህቱ በበኩሉ የሰላም ፋይዳ ብዙ በመሆኑ በኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች መካከል የተጀመረው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ዛሬም እንደወትሮው የሚጠበቅበትን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል። በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ከደርግ ጋር በተካሄደ ጦርነት የተሰዉ 604 ሰማዕታት ፎቶ ግራፎችን ቤተሰቦቻቸው በመያዝ እንዲታወሱ ተደርጓል። ነዋሪዎቹ በሰልፉ ላይ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የትግራይና የተለያዩ ክልሎችን ሰንደቅ ዓላማዎችን በማውለብለብ ለሰንደቅ ዓላማና ለአገራቸው ያላቸውን ክብር ገልጸዋል። በሰልፉ ላይ የታደሙት የከተማዋ ነዋሪዎችም " በኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች መካከል የተፈጠረውን ሰላም እንደግፋለን”፣ "ሁሉም ዓይነት ብሔር ተኮር ጥቃት ይቁም" ፣ "ህግ መንግስቱና የፌደራል ሥርዓቱን ይከበር"  የሚሉ መፈክሮችን አስተጋብቷል። በተመሳሳይ ዜና በትግራይ ምዕራባዊ ዞን የኢትዮጵያና የኤርትራን የሰላም ግንኙነት ለመደገፍ ዛሬ በሁመራ ከተማ ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል። የሑመራ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች በእዚህ ወቅት እንዳሉት ከኤርትራውያን ወድሞቻቸው ጋር የተፈጠረውን ሰላም በዘላቂነት ለማጠናከር  ፍላጎታቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። በድጋፍ ሰልፉ ላይ ህዝቡን ወክለው ንግግር ያደረጉት ነባር ታጋይ ገብረስላሴ ገብረማሪያም እንዳሉት፣ ለዘላቂ ሰላሙ ስኬት ከመሪዎች ባለፈ የሁለቱም አገራት ህዝቦች ተቀራረበው  በጋራ መስራት አለባቸው። ሰላሙ ዘላቂ አንዲሆን ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው በአሁኑ ወቅት ወደህዝብ ለህዝብ እየወረደ ያለው የአገራቱ ግንኙነት እየጎለበት እንዲመጣ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል በሰልፉ ላይ ከተሳተፉ ወጣቶች መካከልም  ወጣት መርሃዊ ገብረማርያም በበኩሉ ለኢዜአ እንዳለው በህገ መንግስቱ  ዜጎች በማንኛውም ቦታ የመኖር ፣ የመዘዋወርና የመስራት መብታቸው በአግባቡ ሊከበር እንደሚገባ ጠይቋል። የከተማው ነዋሪ ወጣት አወጣሽ ተካ በበኩሏ ሁለቱም ህዝቦች ለሰላም ባላቸው ጉጉትና ፍላጎት ምክንያት በአሁኑ ወቅት በተከዜ ድልድይ ማዶ ለማዶ እየተገናኙ ሰላምታ መለዋወጥ መጀመራቸውን ነው የገለጸችው። ይህ የሰላም ፍላጎት ተጠናክሮ ከዳር እንዲደርስ የድርሻዋን በቁርጠኝነት ለመወጣት መዘጋጀቷን ገልጻለች። በሰለፉ ላይ የተሳተፉት በሁመራ ከተማ ከሚኖሩ ኤርትራዊያን መካከልም ወይዘሮ ፍሬወይኒ መኮንን እንዳሉት በሁለቱ አገራት ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ጥረት ደስተኛ ናቸው። ሰልፈኞቹ በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ሞት ጥልቅ ሀዘን ቢሰማቸውም የግድቡ ግንባታ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ሲያደርጉት የነበረውን ድጋፍ አጠናክረው በመቀጠል ጅምራቸውን ከግብ እንደሚያደርሱ አረጋግጠዋል።   የትግራይ ምዕራባዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ ታደሰ በበኩላቸው ለሰልፈኞቹ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት የዞኑ ህዝብ ሰላሙን ለመጠበቅ ላሳየው የማያቋርጥ ትግል ምስጋና ሊቸረው ይገባል። ዛሬም ለሰላም ያለው ቁርጠኛ አቋም በድጋፍ ሰልፉ በድጋሚ ማረጋገጡን ተናግረዋል። " የትግራይ ምዕራባዊ ዞን ህዝብ ከኤርትራ ወንድሞቹ ጋር በቅርበት በድንበር የሚዋሰን በመሆኑም ሰላሙን በእጅጉ ይፈልገዋል" ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው። በኢንጅነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ለሰልፉ ተሳታፊዎች የገለጹት አቶ ኢሳያስ፣  የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዳር እንዲደርስ የዞኑ ህዝብ ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል። በተመሳሳይ በትግራይ ምዕራባዊ ዞን በሚገኙ አራት ወረዳዎች ዛሬ የድጋፍ ሰልፎች መካሄዳቸው ታውቋል።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም