ቀጥታ፡

ለአትሌት ደራርቱ ቱሉ የእውቅና እና የምስጋና መርሐ ግብር ይካሂዳል

መጋቢት 16/2013 (ኢዜአ) ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ በኦሊምፒክ መድረክ በ10 ሺህ ሜትር የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ ላስገኘችው ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ መጋቢት 19 ቀን 2013 የእውቅና እና የምስጋና መርሐ ግብር ይከናወናል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ የእውቅናና የምስጋና መርሐ ግብሩ መጋቢት 19 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ገልጿል።

የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ እንደገለፁት መርሐ ግበሩን ማዘጋጀት ያስፈለገው ለአገር ውለታ የሰሩ ጀግኖችን በሕይወት እያሉ ለመዘከር ታስቦ ነው። 

ደራርቱ በ10 ሺህ ሜትር ውድድር ለአፍሪካ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣች አትሌት በመሆኗ ለዚህ ፈር ቀዳጅ ድል ዕውቅና ለመስጠት መሆኑንም ገልፀዋል።

"ለአገራቸው ጉልበታቸውንና ዕውቀታቸውን የሚሰጡ ዕውቅና ሊሰጣቸው ይገባል" ያሉት አቶ ቢልልኝ ደራርቱ በአትሌቲክሱ ብቻ ሳይሆን በበጎ አድራጎት ተግባርም ትልቅ ቦታ አላት ብለዋል።

አህጉራዊ ጀግና በመሆኗም ሌሎች የእሷን ዓርአያ እንዲከተሉ ለማነሳሳት የዕውቅና መርሐ ግብሩ በር ይከፍታል ብለዋል።

በዕውቅና መርሐ ግብሩ የክልሎች ኃላፊዎች፣ የፌዴሬሽኑ አመራሮች፣ ሚኒስትሮች፣ ታዋቂ አትሌቶችና አርቲስቶች የተካተቱበት ከ600 በላይ ታዳሚዎች እንደሚገኙ ገልፀዋል።

አትሌት ደራርቱ ቱሉ እ.አ.አ 1992 የባርሴሎና ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን በ10 ሺህ ሜትር ውድድር በመወከል በሴቶች ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ አስመዝግባለች።


በተጨማሪም ለኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በዓለም አገር አቋራጭ ውድድሮችና ሻምፒዮናዎች ወርቅ፣ ብር፣ ነሐስና ዲፕሎማ አስገኝታለች። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም