አበበች ጎበና ሆስፒታል የእናቶችና ሕጻናት የጤና አገልግሎት ፖሊሲውን በመደገፍ ጉልህ ሚና ይኖረዋል - ኢዜአ አማርኛ
አበበች ጎበና ሆስፒታል የእናቶችና ሕጻናት የጤና አገልግሎት ፖሊሲውን በመደገፍ ጉልህ ሚና ይኖረዋል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) መጋቢት 16/2013 በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የጀመረው አበበች ጎበና የእናቶችና ሕጻናት ሆስፒታል በመዲናዋ የሕክምና ተቋማት የሚታየውን መጨናነቅ የማቃለል ድርሻው የጎላ መሆኑ ተገለፀ።
የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ አመራሮች በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የጀመረውን የአበበች ጎበና የእናቶችና ሕጻናት ሆስፒታል ዛሬ ጎብኝተዋል።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ የሆስፒታሉ አገልግሎት መጀመር ኢትዮጵያ በእናቶችና ሕጻናት የጤና አገልግሎት ላይ የያዘቸውን ፖሊሲ በመደገፍ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በዘርፉ የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት በማሳደግ በሌሎች መሰል ሆስፒታሎች የሚታየውን መጨናነቅ ከመቀነስ አኳያም ድርሻው የጎላ መሆኑን አክለዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ በጤናው ዘርፍ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት በርካታ ስራዎች እንደሚጠበቁ ጠቁመው፤ በመዲናዋ እንደ አበበች ጎበና የእናቶችና ሕጻናት ሆስፒታል ያሉ የጤና ተቋማት እንዲበራከቱ እገዛ እናደርጋለን ብለዋል።
የሆስፒታሉ ኃላፊና የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት ዶክተር አናኒያ ሰለሞን ሆስፒታሉ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ዕለት አንስቶ በርካታ እናቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ሆስፒታሉ በአጠቃላይ 400 የማዋለጃ አልጋዎች፣ 7 የቀዶ ሕክምና እንዲሁም 18 በምጥ የሚወልዱ እናቶች የሚገለገሉባቸው አልጋዎች እንዳሉት ተናግረዋል።
ይህም ለበርካታ እናቶች አገልግሎት መስጠት ያስችለናል ነው ያሉት።
የሕክምና አገልግሎት ፈላጊዎች ከ16 ጤና ጣቢያዎች ወደ ሆስፒታሉ እንደሚላኩና በቀን እስከ 30 እናቶች በዚያ እንደሚወልዱም ነው የገለጹት።
አበበች ጎበና የእናቶችና ሕጻናት ሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት መስጠት ከጀመረ 20 ቀን ሆኖታል።