በአንድ ማኪያቶ 10 ዶላር እንዲሰባሰብ በበጎ ፈቃደኝነት እሰራለሁ - ታማኝ በየነ

አዲስ  አበባ ሀምሌ 22/2010 በአንድ ማኪያቶ አንድ ሳይሆን 10 ዶላር እንዲሰባሰብ በበጎ ፈቃደኝነት እንደሚሰራ ታማኝ በየነ ገለጸ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በዋሽንግተን ዲሲ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር ትናንት ማምሻውን ተወያይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር እንዲያደርጉ ተጋብዘው ሳለ ንግግራቸውን በማቋረጥ አክቲቪስት ታማኝ በየነን ወደ መድረክ በመጋበዝ ንግግር እንዲያደርግ አድርገዋል። ታማኝ በየነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ማህበረሰብ ከአንድ ማኪያቶ አንድ ዶላር እንዲሰጡ ጥያቄ ማቅረባቸውን በንግግሩ አስታውሷል። ይህን ጥሪና ኃላፊነት በመቀበል በአሜሪካና በመላው ዓለም ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከአንድ ማኪያቶ አንድ ዶላር ሳይሆን ከአንድ ማኪያቶ 10 ዶላር እንዲሰባሰብ ለማድረግ የአስተባባሪነት ሃላፊነት ወስዶ በበጎ ፈቃደኝነት እንደሚሰራ ተናግሯል። ከዳያስፖራው ገንዘብ በማሰባሰብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮች ለአገራችን እናስገባለን ብሏል። በአግባቡ ከተቀምንበት ኢትዮጵያን መለወጥ የሚችል ማህበረሰብ በመላው ዓለም እንዳለና ዳያስፖራው ኢትዮጵያዊ ለአገሩ ትልቅ አቅም እንደሆነ ነው ታማኝ የገለጸው። “ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሁሉንም ኃላፊነት አንሰጥም መንገዱን አሳይተውናል ሁላችንም ለተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል የበኩላችን አስተዋጽኦ ማበርከት አለብን” ብሏል። በዚህ ረገድም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚያከናውኗቸው ስራዎች ከጎን በመሆን ለመስራትና ለማገልገል በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ቃል እንደሚገባም ገልጿል። በኢትዮጵያ አሁን እየመጣ ላለው ለውጥ መስዋዕት የሆኑ ሰዎችም ክብር እንደሚገባቸው አስገንዝቧል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ "ስትደመሩ የዓለም ህዝብ እጁን ይሰጣችኋል" የዋሽንግተን ዲሲ ከተማ የሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓ.ም  ''የኢትዮጵያዊያን ቀን'' አደርጎ መሰየሙ የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል። ቅጥር ገንብቶ በግንብ የታጠረ ሳይሆን የተደመረ፣ በድልድይ የተቀራረበና ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ኩራት የሆነች ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ከተፈለገ በይቅርታ መደመር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ኢትዮጵያዊነት የተሸመነበት ድርና ማግ ባለ አንድ ቀለም ነጠላ ሳይሆን በህብረ ቀለማት ያሸበረቀ፣ አውታረ ብዙና ጥበብ ያለው እንደሆነም አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ዘርና ሃይማኖት የማይለያየው በእምነት ድልድይ ተሻግሮ የሚዛመድ እንደሆነም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስረዱት። ለኢትዮጵያ ከገንዘባችሁ በላይ ጊዜያችሁን፣ ልባችሁንና ፍቅራችሁን በመስጠት ለሁላችሁ እናት ለሆነች አገር መስራት ይገባል ብለዋል። የተቋቋመው የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በገለልተኛ አካል እንደሚመራና ለዚህም ታማኝ ሰዎች እንዲመሩት መወሰኑን ጠቁመዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም