የወጣቶች የስነ- ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ትኩረት እንደሚሻ አንድ ጥናት አመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
የወጣቶች የስነ- ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ትኩረት እንደሚሻ አንድ ጥናት አመለከተ
መጋቢት 16/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የወጣቶች የስነ- ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አንድ ጥናት አመለከተ።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የወሊድ ምጣኔ ካላቸው የአፍሪካ አገራት ቀደሚ ስትሆን ካለት ህዝብ 33 ነጥብ 8 በመቶ ወጣት፣ 26 በመቶ ደግሞ ከ20 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይህም አገሪቱ የወጣት ህዝቧን የጤና ሁኔታ ለማሻሻል አበክራ መስራት እንዳለባት አመላካች ነው።
በዚሁ ዙሪያ ጤና ሚኒስቴርና ማሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል በጋራ ''ለወጣቶች'' በሚል በፓርክ ፋውንዴሽን ድጋፍ ለሁለት ዓመት ሲደረግ የነበረውን ጥናት ዛሬ ይፋ ሆኗል።
የጥናቱ አቅራቢ አቶ መልካሙ ተሾመ እንዳሉት በርካታ ወጣት ሴቶች ስለ ስነ-ተዋልዶ ጤና ጉዳዮችና እርግዝናን እንዴት መከላከል እንደሚችሉ በቂ መረጃ የላቸውም።
የግል ጉዳያቸው ተላልፎ ይሰጥብናል በሚል፣ ከእምነት ጋር ፣ አገልግሎት ሰጪዎቹ አላዋቂ ያደርጉናል በሚል የተሳሳተ ምክኒያት ወጣቶቹ አገልግሎት የማግኘት ፍላጎታቸው አናሳ ይሆናል።
እነዚህ ተግዳሮቶች በአለም አቀፍ ደረጀ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ሳቢያም ተባብሰው ቀጥለዋል።
በአፍላ ወጣቶች የስነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ሰጪዎችና የመረጃ ተቀባዩ አለመግባባት የባህሪና የፍላጎት አለመጣጣም ለችግሮቹ መንስኤ መሆኑን ጠቁመዋል።
ስለዚህም ወጣቶቹ ላልተፈለገ እርግዝና፣ ለጽንስ ማቋረጥና ለሌሎች ተዛመጅ ችግሮች ይዳረጋሉ ብለዋል።
ስለዚህም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትና ባለድርሻ አካላት ጉዳዩን በአንክሮ ተመልክተው መፍትሄ መስጠት አለባቸው ብለዋል።
በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና የህጻናት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም እንዳሉት መንግስት የአፍላ ወጣቶች ጤና የማበልጸግ ስራን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
ሚኒስትሩ የወጣቶችንና አፍላ ወጣቶች ጉዳይ በአምስት አመቱ የጤና ዕቅድና በአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ውስጥ እንዲካተት ተደርጎ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይ ወጣቶች በሽታን አስቀድሞ በመከላከል ስራ ላይ እንዲያተኩሩና የጤና ሁኔታቸው እንዲሻሻል የጤና ኤክስቴሽን ባለሙያዎችን አቅምና የመረጃ ተደራሽነት የማጎልበት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር ወደ 72 በመቶ ዝቅ በማድረግ፣ የህጻናትን ሞት ደግሞ ወደ 62 በመቶ ዝቅ በማድረግና የስነ-ተዋልዶ ጤናን በማሻሻል ባለፉት አመታት ውጤት ማስመዝገቧን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የማሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል ዳይሬክተር አቶ አበበ ሽብሩ በበኩላቸው የስነ ተዋልዶ ጤና ላይ አተኩሮ መስራት ለአንድ አገር የማህበራዊና ኢኮኖሚ እድገት ዋስትና ነው።
ስለዚህም አገራት በአፍላ ወጣት ጤና አገልግሎት ላይ ትኩረት ስጥተው መስራተ አለባቸው ብለዋል።