ቀጥታ፡

በህገ ወጥ መልኩ በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገፆች እየተዋወቁ ያሉ ማሟያ ምግቦች የጤና እክል ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ተጠቆመ

አዲስ አበባ መጋቢት 16/2013  (ኢዜአ) በህገ ወጥ መልኩ በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገፆች እየተዋወቁ ያሉ ማሟያ ምግቦች ለተለያዩ ህመሞች ሊያጋልጡ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ የምግብ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አሳሰበ።

ቴሌግራምን ጨምሮ በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገፆች በህገ ወጥ መንገድ የሚዘዋወሩና የሚተዋወቁ ማሟያ ምግቦች (food supplement) ደህንነታቸው ያልተረጋገጠና ያልተመዘገቡ መሆናቸውንም ባለስልጣኑ አስታውቋል።

በመሆኑም ማህበረሰቡ መዲሃኒቶቹን ያለባለሙያ ትእዛዝ ከተጠቀመ ለኩላሊት መድከም፣ የጉበት ህመምና ሌሎችም ተዛማጅ በሽታዎች ሊጋለጥ ይችላል ብሏል ባለስልጣኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫው።

ባለስልጣኑ በአዋጅ ቁጥር 1112/2011 በተሰጠው ስልጣን መሰረት የምግብ ጥራት ድህንነት እና የመድሀኒትና የህክምና መሳሪያዎችን ጥራት ድህንነት ፈዋሽነት ይቆጣጠራል።

በባለስልጣኑ እውቅና ሳያገኙና ደህንነታቸው ሳይረጋገጥ "ለውፍረትና ሌሎችን ጥቅሞችን ያመጣሉ" በሚል በህገ ወጥ መንገድ የማሟያ ምግቦችን የሚሸጡ ግለሰቦች መኖራቸውን አረጋግጠናል ብሏል።

በተለይም ፕሮቲን ቪታሚን እና ሌሎችም ማሟያ ምግቦች በቴሌግራምና ሌሎች ማህበራዊ ድረ ገፆች እየተዋወቁና እየተሸጡ መሆኑንም ደርሰንበታል ብሏል በመግለጫው።

እነዚህ በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ማሟያ ምግቦች በባለስልጣኑ ተመዝግበው ፈቃድ ሲያገኙ ብቻ መሸጥ እንደሚችሉ ባለስልጣኑ አስታውቋል።

በፋርማሲና ልዩ ሱቆች ለሽያጭ ቀርበው በባለሙያ ምክር መሰረት ብቻ መወሰድ ያለባቸው መሆኑንም ገልጿል።

ምርቶቹን ያለ አግባብ መጠቀም ለኩላሊት መድከም የጉበት ህመምና ሌሎች ከባድ የጤና እክሎች ሊያጋልጡ ስለሚችሉ ማህበረሰቡ መጠንቀቅ እንዳለበት ባለሰልጣኑ አሳስቧል።

ማሟያ ምግብ የሚባለው ከምግብ ውስጥ የጎደለውን ንጥረ ነገር ለማቅረብ በማሰብ በህክምና ባለሙያ ትእዛዝ የሚወሰድ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በህገ ወጥ መንገድ የሚዘዋወሩ የምግብ መድሃኒትና የጤና ግብዓቶችን በጋራ ለመከላከል ህብረተሰቡ በነፃ የስልክ መስመር 8482 ጥቆማ እንዲሰጥም ጥሪ አስተላለፏል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም