ቀጥታ፡

የምክር ቤቱን አሰራር በጣሰ መልኩ በወገንተኝነት የሚነሱ ሀሳቦች ተቀባይነት የላቸውም--የምክር ቤቱ አባላት

መጋቢት 16/2013 (ኢዜአ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሰራርን በጣሰ መልኩ በወገንተኝነት የሚነሱ ጥያቄዎችና ሀሳቦች ተቀባይነት የላቸውም ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የምክር ቤት አባላት ተናገሩ።

 የምክር ቤቱ አባላት ተስማምተው ያጸደቁትን የጥላቻ ንግግር አዋጅ ተግባራዊ በማድረግ ለሌላው አርአያ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ባለፈው ማክሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።

በዚሁ ጊዜ አንዳንድ አባላት ከምክር ቤቱ የአሰራር ስነ-ምግባር ውጪ ሀሳቦችን በስሜታዊነት መሰንዘራቸው ተገቢ አለመሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል።

የምክር ቤቱ አባል አቶ ጫላ ለሚ እንደሚሉት የፓርላማ አባላት በወከሉት ህዝብ ላይ የሚደርስ በደል እንዲታረም መጠየቃቸው ከሃላፊነት ባለፈ ግዴታ ጭምር ነው።

ይሁንና አንድ የምክር ቤት አባል ሀሳቡን ከስሜታዊነት በጸዳና የህዝቡን ስነ-ልቦና በማይጎዳ መልኩ ማንሳት ይገባዋል ብለዋል።

ሌላዋ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ አገሬ ምናለ አንዳንድ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቧቸው ሀሳቦችና ጥያቄዎች የምክር ቤቱን የአሰራርና የአባላት ስነ-ምግባር ደንብ የጣሰ መሆኑን ይገልጻሉ።

የምክር ቤት አባላት ተስማምተው ያጸደቁትን የጥላቻ ንግግር አዋጅ ተግባራዊ በማድረግ ለሌላው አርአያ መሆን እንዳለባቸውም በማስገንዘብ።

ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ አያሌው አይዛ ''ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁኔታ አኳያ የህዝቦችን አንድነት የበለጠ የሚያጠናክርና ሰላምን የሚያመጣ እንጂ ከፋፋይ ሀሳብ የሚሰነዝር አያሻትም'' ብለዋል።

የምክር ቤት አባላት ለሰላም ግንባታው ዋነኛ የመፍትሄ አካል ሆነው በመስራት አሁን እየታየ ያለው ጊዜያዊ ችግር የሚፈታበትን አቅጣጫ መጠቆም እንጂ ችግሩን ማባባስ የለባቸውም ብለዋል።

የምክር ቤት አባል ወይዘሮ አስካል ጥላሁንም የምክር ቤት አባላት የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች በደል የሚቆረቁረው ከወገንተኝነት የጸዳ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

''ከተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ተወክለን የመጣን እንደመሆናችን የአካባቢያችንን ችግር አግዝፈን የሌላውን አኮስሰን ማንሳት ተገቢ አይደለም'' ብለዋል።

የምክር ቤት አባላት የሚሰነዝሯቸው ሀሳቦች በትክክለኛ ማስረጃ የተደገፈና ከሚመለከተው አካል ማረጋገጫ የተሰጠው ሊሆን እንደሚገባም ነው የገለጹት።

የምክር ቤት አባላት ያላቸውን ቀሪ ጊዜ በምክር ቤቱ አሰራርና የአባላት ስነ-ምግባር ደንብ መሰረት ስራቸውን በማከናወን የተጣለባቸው ሃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም