ያሁኑ ይባስ!

50
በእንግዳው ከፍያለው /ኢዜአ/ በዓለም ላይ የበርካታ ጀግኖች ደም በከንቱ ፈሷል። በአሜሪካ ለጥቁሮች መብት የቆመው የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ጆንኤፍ ኬነዲ፣ “ህልም አለኝ” በሚል ሳቢና መሳጭ ንግግራቸው የሚታወሱት የጥቁሮች መብት ተሟጋች ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ የህንድ አባት የሚባሉት የሰላም ታጋይ ማህተመ ጋንዲን…ከብዙ በጥቂቱ መጥቀስ ይቻላል። በአገራችንም እነ በላይ ዘለቀን የመሰሉ አርበኞች ባደባባይ ተሰቅለዋል፤ እነ ግርማሜ ነዋይ በምዕራባውያን የለውጥ እንቅስቃሴ ተማርከው በአገራቸው ለመተግበር እንቅፋት የሆነውን ስርዓት ለማስወገድ ያደረጉት መፈንቅለ መንግስት ሳይሳካ ቀርቶ ተገለዋል። በአገራችን 60 ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና ባለስልጣናት በአንድ ጊዜ በደርግ ሲጨፈጨፉ የዓለም መገናኛ ብዙሃን “ኢትዮጵያ የጦር መሃንዲሶቿን በራሷ እጅ አጠፋች’’ ብሎ ዘግቧል። በየአደባባዩና በየጥሻው እየተገደሉ የሚገኙት፣ የት እንደደረሱ ሳይታወቅ ለቤተሰብ የእግር እሳት ሆነው የቀሩ ስንቶች እንደሆኑ ፈጣሪ ይቁጠራቸው። ድሮ ከስልጣንና ከመብት ጋር ተያይዞ ነበር በአገራችን የሚፈጸሙት ወንጀሎች። አሁን ደግሞ የኢኮኖሚ አምባሳደሮቻችን ላይ ተከታታይ ጥቃት መፈጸም ተጀምሯል። የት እንደተጀመረ? ወደየት እንደሚያመራ? ምን ያህል ሰው እንደተነጣጠረ? በማን እንደሚቆም? … ማንም የሚያውቅ የለም። ለማሰብም ከአእምሮ በላይ የሆነ ሰይጣናዊ ትውፊት ያለበት ረቂቅ ስራ እየሆነ መጥቷል። ባለፈው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ስራ አስኪያጅ ሚስተር ከማር ከጸሃፊያቸው ጋር በመኪናቸው እየሄዱ ተገደሉ የሚለውን ዜና ስንሰማ ሰውየው የውጭ አገር ዜጋ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ግራ ተጋብተን ነበር። ማን እንደገደላቸው? ምክንያቱ ምን እንደሆነ? ከጀርባ ምን እንዳለ? አልታወቀም። የምርመራው ውጤት ገና ነው።ሰኔ 16/2010 ዓ.ም በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ ሳይሳካ ቢቀርም በንጹሃን ወገኖቻችን ላይ ያደረሰው ጉዳይ ቀላል የሚባል አይደለም። “ያሁኑ ይባስ!” አለ ያገሬ ሰው። የኢንጅነር ስመኘው በቀለን ሞት የሰማ ሰው ያሁኑ ይባስ ከማለት ውጭ ምን ሊል ይችላል? የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ስራ ከጀመሩ አንስቶ እኔ በስራ አጋጣሚ አምስት ጊዜ ያህል ወደ ታላቁ ኢትዮጵያ ህድሴ ግድብ በመጓዝ አራት ጊዜ አግኝቻቸዋለሁ። ኢንጅነር ስመኘው ሁል ጊዜም የሚሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጵያን የወደፊት ራዕይና ስኬት፣ የህዝቡን የአንድነት መንፈስ፣ የሰራተኞችን ታታሪነት… ከሌላው ዓለም ጋር እያነጻጸሩ አንድ የአገር መሪ ከሚገልጸው በላይ ሳይንሳዊ ትንታኔ በመስጠት የሄደውን ህዝብ በሙሉ የግድቡ አምባሳደር አድረገው ሹመው ይልሱታል። የእርሳቸውን መልዕክት የሰማው ሰውም አዲስ መንፈስና ወኔ በመሰነቅ በቦንድ ግዢ፣ በገንዘብ መዋጮ፣ በችግኝ ተከላና ሌሎች ስራዎች የራሱን ሚና ይወጣል፤ ሌላውም እንዲወጣ ያስተባብራል፣ ይደግፋል፣ ይመራል…። በዚህም ምንም እንኳ አገራችን ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት የሰላም መታወክ ችግር ቢገጥማትም በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያለው የአገሬ ህዝብ ቦንድ ከመግዛት ገንዘብ ከመለገስ ለአፍታም አለመዘናጋቱ የታየ ጉዳይ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ የሚገነባው የጉባና ሲርባባ ወረዳዎች አዋሳኝ ላይ ነው። ቦታው የአባይ ወንዝ ወደ ሱዳን ድንበር የተጠጋ በመሆኑ ሙቀቱ ከ40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ ነው። ለጉብኝት የሚሄደው ህዝብ እንኳን ሰውነቱ የእጁ መዳፍ ላይ ላቡ ሲንጠባጠብ ይታያል። አንዳንዱ ሰው በከባዱ ሙቀት የተነሳ ግንባሩና ትክሻው እንደ ሙዝ እንደሚላላጥ አይቻለሁ። የልማቱ አርበኛ፣ የህዳሴው ጀግና… ኢንጅነር ስመኘው ግን እንኳን ላብ ከግንባራቸው ሊወጣ አንደበታቸው ማመንጨት ከሚገባው በላይ የህዳሴ መልዕክት እያፈለቀ የሄደውን ህዝብ ወኔ ማስታጠቁን ለአፍታም ቢሆን አያቋርጥም። ሁልጊዜም አገራዊ ነባራዊ ሁኔታውን ከዓለም አቀፍ ነባረዊ ሁኔታ ጋር እየቃኘ የሚሰብክ ከእርሳቸው ውጭ እስካሁን አላየሁም። ኢንጅነሩ ሁልጊዜ ንግግራቸውን ሲጀምሩ “በዚህ ጊዜ በዓለም ላይ ህዝብ ከራሱ ኪስ እያዋጣ የሚገነባው ታላቅ ፕሮጀክት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክተሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት ነው፤ በዚህም ሁላችንም ልንኮራ ይገባል’’ በማለት ንግግራቸውን ይጀምራሉ። አሁን ከኪሳችን እያዋጣን የምንገነባው ነገ ታላቅ ደመወዝ ከፋይ አገር ለመፍጠርና የእያንዳንዱን የነፍስ ወከፍ ገቢን ለማሳደግ ነው በማለት ያክላሉ። ያኔ የሄደው ሰው ሁሉ ሙቀቱንና ድካሙን ረስቶ በኩራትና በወኔ መንፈሱን ያድሳል። እንገነባዋለን! ሌላም እንደግማለን! ታሪካችንን እናድሳለን፣ እንለውጣለን!... የሚል የሞራል ልዕልናን እንዲጎናጸፍ የሚያደርጉ የልማት አርበኛ ናቸው ኢንጅነር ስመኘው። ግድቡ ከሚገነባበት ከመሃል አገር ሲሄድ በግራ በኩል ተመልካች ሁሉ ግድቡ ያለበትን ሁኔታ በግልጽ የሚያሳይ አንድ ቦታ ተዘጋጅቷል። ግድቡ እያደገ ሲሄድ የማሳያ ቦታዋም ወደ ላይ ከፍ ትላለች። የግድቡን ማደግ ተከትሎ ኢንጅነሩ የተራራውን ሰንሰለት ተከትለው ሌላ ማሳያ ቦታ ያዘጋጃሉ፡፡ ለማሳያ የተመረጠው ቦታም መኪና እንደ ልብ የሚገባበት በመሆኑ የሄደውን እንግዳ መኪናቸው ውስጥ ሆነው የሚመሩት እራሳቸው ናቸው። መንገዱ አዲስ አበባ እንደሚገኘው የጎተራ መንገድ የተጠላለፈ በመሆኑ ያለ መሪ ምን አልባት ሲዞሩ መዋል ካልሆነ በስተቀር የታሰበውን ቦታ ማግኘት እንኳን ለእንግዳ በቦታው ለሚሰራም ይከብዳል። ኢንጅነር ስመኘው “ግድቡ 155 ሜትር ከፍታ ይኖረዋል፤ ከተራራው እስከ ተራራው ጫፍ 1ሺህ 780 ሜትር ርዝመት ይኖረዋል። ከተራራው ጀርባ የአምስት ኪሎ ሜትር ሳድል ዳም ግንባታ በመካሄድ ላይ ነው። ይህ ማለት ግድቡ ውሃ መያዝ ሲጀምር በዛ በኩል ያለው ዝቅ ያለ ቦታ በመሆኑ እንዳይፈስ ነው የሳድል ግድቡ ግንባታ አስፈላጊነት” እያሉ ይቀጥላሉ። “የታላቁ የኢተዮጵያ ህዳሴ ኤልክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በውሃ ሲሞላ ከ246 ኪሎ ሜትር በላይ ወደ ኋላ ተጉዞ ውሃው ይተኛል። ለዚህም ደኖች በኋላ ውሃውን ለትነት እንዳይዳርጉ የመመንጠር ስራ ተሰርቷል። ውሃው የሚሸፍነው ቦታ አንድ ሺህ 874 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ግድቡ ሲጠናቀቅ 6ሺህ 450 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ የሚያመነጭ በመሆኑ የምስራቅ አፍሪካን በሃይል ልማት ለማስተሳሰር ሚናው የጎላ ነው” ይላሉ። ማስታወሻ ይዘው እንዳይመስላችሁ። ጣታቸውን ወደ ግድቡና ወደ ተራራው እንዳመለከቱ ነው ግድቡ ያስፈለገበትን ሁኔታ፣ አሁን የደረሰበትን፣ ቀሪ ስራዎች፣ የሰራተኛውን ሁኔታ… የሚተነትኑት። እንደሚታወቀው ብለው ይቀጥላሉ ኢንጅነር ስመኘው “የሲቪል ስራው በጣሊያኑ ሳሊኒ ኢምፕሬጅሎ ኤስ ኤ እየተገነባ ሲሆን የኤሌክትሪክና ሃይድሮሊክ ስትራክቸር ስራዎችን የሚሰሩት በኢፌዴሪ ብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን አማካኝነት እየተካነወነ ይገኛል” በማለት ይጨምራሉ። ከ10 ሺህ በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ሰራተኞች እየተሳተፉበት የሚገኝ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነ ፕሮጀክት ነው በማለት ንግግራቸውን ያጠቃልላሉ። አርበኛ ሁልጊዜም ውሎ አዳሩ በረሃ ነው። ኑሮውም ዱር ቤቴ ብሎ ነው። አድኖ ይበላል፤ ያገኘውን ይለብሳል… ለእርሱ ሁል ጊዜም የሚያሳስበው የወጣበት ጉዳይ ነው። አገር ተደፈረች ብሎ ከሆነ የወጣው ጠላቶቹን እንዴት እንደሚበቀል ሌት ከቀን ይጥራል። የአካባቢውን ማህብረሰብ በማስተባበርና በመምራት አለኝታና መከታ ይሆናል። ህዝቡም ከጠላት እጅ ለመውጣት ወይም ለመከላከል ሲል ዱር ቤቴ ብሎ የወጣውን አርበኛ በመደገፍ ከጠላት ጋር ይዋጋል፤ ይፋለማል። ኢንጅነር ስመኘውም ውሎ አዳራቸውን በጉባና ሲርባባ ወረዳዎች ባለው በረሃ ካደረጉ ሰባት ዓመት የሆነው የልማት አርበኛ ናቸው። የጀመረው ፍልሚያ ደግሞ ከድህነትና ኋላቀርነት ጋር ነው። ግንባሩም ጉባና ሲራራ አዋሳኝ ያለው የአባይ ወንዝ። ከድሃ አገር ተፈጠሩ፣ ከድሃ ህብረተሰብ ተገኙ፣ የራሳቸውን መብላትና መጠጣት ለእርሳቸው ምንም አይመስላቸውም…። የተፈጥሮ ሀብትን ውሃውን፣ መሬቱን፣ ደኑን… አሻግሮ እያየ የሚራብ ህዝብ፣ ደሃ አገር… ማየት አልዋጥላቸው ብሏል። እናማ የድህነትን አከርካሪ በሙያቸው ለመስበር እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ያለ አማራጭ የለም። የተሰጣቸውን ሃላፊነት በበጎ ተቀብለው በረሃ ሲወርዱ ሁልቆ መሳፍርት ሳንካ እንደሚገጥማቸው ለአፍታም ቢሆን የሚጠራጠሩ አይመስለኝም። ነገር ግን አሁንና በዚህ መልኩም ይሆናል ብሎ ማሰብና ማመን ደግሞ ለማንም የሚዋጥ አይሆንም። ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከመምህራን ጋር ባካሄዱት ውይይት ይመስለኛል የህዳሴው ግድብን በተመለከተ ከተሳታፊዎች የተነሳላቸውን ጥያቄ ተከትሎ አንዳንድ ማብራሪያ ለመስጠት ሞክረዋል። ይህን ተከትሎም የተለያዩ ሰዎች በውስጣቸው የሚያስቧቸውን ነገሮች ማሰላሰል ጀምረዋል። ግልጽነት ያልታየባቸው አሰራሮች ይኖራሉ ያሉም አልጠፉም። የውጭ መገናኛ ብዙሃንም የግድቡ አፈጻጸም ሪፖርት ለህዝብ ይፋ ሲሆን የፋይናንስ ሪፖርቱ ለምን አይገለጽም የሚሉ እንደነበሩ አስታውሳለሁ። ይህን የሰማው አንድ ጓደኛዬ የሆነ ችግር ሊኖር እንደሚችል ሲነግረኝ መቀበል ተስኖኝ ነበር።ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ዙሪያ ያለውን ክፍተት ለማሳየት ሲሞክሩ አንዳች መነሻ ሊኖራቸው እንደሚችል እርግጥ ነው። ከግድቡ ግንባታ ጋር ተያይዞ ሊስትዋሉ የሚችሉ ስር የሰደዱ ሰው ሰራሽ ችግሮችን ደግሞ ባንድም በሌላም መንገድ እኚሁ መሐንዲስ ማወቃቸው አይቀርም። ስለዚህም ጉዳዩ ዞሮ ዞሮ የአጥፊዎች ጥርስ ውስጥ ይከታቸዋል የሚለው ሃሳብ አእምሮዬ ውስጥ ተሰንቅሮብኝ ከጓደኛዬ ጋር ተለያየን ። ዳግመኛ ጓደኛዬ ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ አንስተን ሳናወራ ዛሬ ጧት የማህበራዊ ሚዲያ ሲከታተል የነበረ የስራ ባልደረባዬ “ኢንጅነር ስመኘው ተገደሉ’’ የሚል ዜና አይቼ ላረጋግጥ ስል መብራቱ ጠፋ ብሎ እየተርበተበተ መጣ። እኔም በፌስቡክ ከሆነ ወሬ ነው፤ እንዴት ሊሆን ይችላል? እንዴትስ ሊታሰብ ይችላል? ሊታሰብም ሊሆንም አይችልም! አልኩ ፈርጠም ብዬ። የስራ ባልደረባዬም ሆዱን ባር ባር ብሎት ቆይቶ አንገቱን እንደደፋ ከቢሮዬ ወጣ። አእምሮዬ ግን ማሰላሰሉን፣ ማሰቡን፣ ማውጠንጠኑን… አልተወም። እንደምታውቁት የዛሬ መብራት ሲመጣ ሲሄድ ነው፡፡ አዳሩንማ የባሰ ነው እንዳትሉኝ፤ ብትሉኝም አይገርመኝም፡፡ ምሽት ላይ ስለማየው። የዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ፈረንሳይ ከክሩሹያ ያደረጉትን ጨዋታን እና ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድና የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በሚሊኒየም አዳራሽ ያደረጉትን ንግግር በመብራት መጥፋት ምክንያት ሳንከታተል መቅረታችን የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ሲሄድ ሲመጣ የማይደክመው መብራት ትንሽ ቆይቶ መጣ። እኔም ተቻኩዬ የኮምፒዩተሬን መክፈቻ ተጫንኩትና የኢንተርኔት ገመዱን ሰካሁ። የመግቢያ የሚስጥር ቁጥሬን አስገብቼ ትንሽ ከጠበኩ በኋላ ሙሉ በሙሉ ተከፈተ። በፍጥነት ፌስ ቡክ ስከፍት በርካታ ሚዲያ የኢንጅነር ስመኘውን ሞት ዘግቦታል። ከመደንገጤ የተነሳ ከጠረፔዛው ላይ ተደፍቼ ቀረሁ። ጧት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ አባልና የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ሃላፊ የሆኑትና አሁን እየታየ ያለው ለውጥ የጀርባ አጥንት ተብለው የሚጠቀሱት የአቶ ተስፋዬ ጌታቸውን ሞት ስሰማ በሃዘን የታመመው ራሴ አሁን ጠረፔዛ ላይ ተደፍቷል። የበረሃውን የልማት አርበኛ ሞት ስሰማ የምቋቋምበት ምን አይነት ወኔ ይኑረኝ? አሁን ምን ሊያጋጥም እንደሚችል እንደቀልድ ስናወራው የነበረው ተራ መላ ምት እውን ሆኗል። የኢንጅነሩን መሞት ሃምሌ 19/2010 ዓ.ም ረፋድ ላይ ማህበራዊ ሚዲያውና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን ዜናውን መቀባበል ይዘውታል። ግራ የሚያጋባው ነገር ኢንጅነር ስመኘውን ያህል ታላቅ የልማት አርበኛ እንዴት ሹፌር የለውም? ጥበቃ እንዴት አልተመደበለትም? የሚለው ጉዳይ ነው። የክልል ባለስልጣናት ጥበቃ ሲመደብላቸው ይህን የመሰለ ጀግና እንዴት የለውም? የሚለው ጥያቄ አሁንም አልተመለሰም። ፖሊስና የብሄራዊ ደህንነትም ሙያዊ ብቃቱ የሚፈተሽበት ጊዜ ላይ ነው። የውጭ ሀገር የወንጀል ምርመራ ተቋማትም ጭምር የእኚህን የአገር ጀግና ሞት አጣርተው ወንጀሎኞች በቅርብ ቀን ለፍርድ ሊቀርቡ የሚችሉበትን መንገድ ለያፋጥኑት ይገባል። ህብረተሰቡና የሚመለከተው አካል ሁሉ መረጃ በማቀበል አጋርነቱን ሊያሳይ ግድ ይለዋል። ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይፈጸምም በየአካባቢው ያለው ወጣት ነቅቶ ሊጠብቅ ይገባል የሚል መልዕክትም አለኝ። የጀግናችን ሞት ከእርምጃችን ለአፍታም አያግደንም፤ ወንጀለኞቹ ማንም ይሁኑ ማን በራሳቸው ላይ እባብ እንደጠመጠሙ ይቁጠሩት። ወንጀለኛ ሁልጊዜም ሚስጥር ከማጥፋት ወደ ኋላ አይልም። የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረውን አንድነት፣ ፍቅር፣ ልማትና መደመር አጠናከሮ በማስቀጠል የብልጽግና ቁንጮ ላይ ከመድረስ ወደ ኋላ አይልም።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም