ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሳይንስ ባህል ለመፍጠር ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ ትውልድ ላይ ማስረጽ ይገባል

አዲስ አበባ (ኢዜአ)  መጋቢት 16/2013 በኢትዮጵያ የሳይንስ ባህል ለመፍጠር ከቅድመ መደበኛ ትምህርርት ጀምሮ በትውልድ ላይ ማስረጽ እንደሚገባ የሳይንስ ምሁራን ተናገሩ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በመተባበር ከአገር ውስጥና ከውጭ አገራት የሳይንስ ሊቃውንት በበይነ መረብ የተሳተፉበት 'የሳይንስ ፖሊሲና ስትራቴጂ ለኢትዮጵያ ብልጽግና' የተሰኘ የምሁራን መድረክ አካሂዷል።

የመድረኩ ጥሁፍ አቅራቢዎችም የሳይንስን ባህል በማኅበረሰቡ ዘንድ ለማስረጽ ጊዜ የሚጠየቅ በመሆኑ፣ ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ብቃት ያለው የሳንይስ ትምህርት መዘርጋት ፋይዳው ሁለንተናዊ መሆኑን ገልጸው፤ በሳይንስ ብቃት ያለው የሰው ሀብት መገንባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በሳይንስ ብቃት ያለው የሰው ሀብት ከአንድ አገር ጥቅል ዓመታዊ ገቢ እመርታ ጋር የሚተሳሰር ነው ይላሉ።

ጥራት ባለው የሳይንስ ትምህርት እነ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓንና ሲንጋፖርን ለአብነት በማንሳት ከችግር ተስፈንጥረው ስለመውጣታቸው፣ በፖለቲካና በዴሞክራሲም የተረጋጉ እንደሆኑ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የሳይንስ ትምህርት ስርዓቷን መመርመር እንዳለባት፤ በትምህርት ተቋማት ሽፋን ሳይሆን ጥራት ላይ ማተኮር፣ ለሳይንስ በቂ በጀት መያዝና የሳይንስ ባህልን የሚገነባ ፖሊሲ ገቢራዊ ማድረግ ይጠይቃል።

ሳይንስ ባህል እንዲሆን ደግሞ ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ በትውልድ ላይ ማስረጽ ያሻል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያም የተሻለ ዓለም ለመፍጠር፣ ወይንም የነበረውን ተፈጥሮ ለማስቀጠል በሳይንስና ቴክኖሎጂ እመርታ ማምጣት ያስገድዳል ይላሉ።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የማኅበረሰቡን አኗኗር ለማሻሻል፣ በሁሉም መስክ አገራዊ እድገትና ብልጽግና እንዲመጣ ጥናትና ምርምር ለማካሄድ፣ ሳይንስን ለማስረጽና መንግስትን ለመደገፍ የተቋቋመ የምሁራን ቤት መሆኑን ነው የገለጹት።

"ዛሬ ከሳይንስ ውጭ የሆነ ነገር የለም" የሚሉት ፕሮፌሰሩ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ማኅበረሰብ የተሳሰሩ በመሆናቸው ሳይንስን ባህል ያደረገ ትውልድ መፍጠር ይገባል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ስነ-ባህሪ ኮሌጅ ባልደረባ ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ በበኩላቸው፤ ለሳይንስ መዳበር ትምህርቱ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ መሰጠት አለበት ሲሉ ሃሳቡን ይደግፋሉ።

ሳይንስና ቴክኖሎጂ ካልዘመነ አገራዊ ዕድገትና ብልጽግና እንደማይረጋገጥ ጠቅሰው፤ በዘርፉ በስፋት ሊሰራበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የሳይንስና ከፍትኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ምድረ ቀድምት አገር ብትሆንም ሳይንስን በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ግልጋሎት የማዋል ልማድ አናሳ እንደሆነ ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ የሰው ሀብት፣ የመሰረት ልማት፣ የበጀትና ቅንጅታዊ አሰራር ችግሮች ምክንያቶች እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

'ሳይንስ ባደጉት አገራት የዕድገት መሰረት ነው' የሚሉት ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዘርፉን ለማዘመን የሳይንስ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርጻ ወደ ትግበራ መግባቱን ገልጸዋል።

የሳይንስ ፖሊሲው በሰው ሀብት ብቃትና በዕውቀት ሀብት አያያዝ፣ በመሰረተ ልማትና ግብዓት፣ በአስተዳደር፣ በምርምርና ፈጠራ፣ በፋይናንስና ማበረታቻዎች፣ ትብብርና አጋርነት አትኩሯል ብለዋል።

ለዚህ ስኬት ደግሞ የሳይንስ ባህል ለመፍጠር ዕውቅ የሳይንስ ምሁራን የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም