ቀጥታ፡

የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ከህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የሚሰጣቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች ተግባራዊ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

መጋቢት 16/2013/ኢዜአ/ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ከህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የሚሰጣቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች ተግባራዊ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አሳሰበ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበኩሉ የአስተዳደር በደልን በተመለከተ የሚሰጠውን የመፍትሄ ሃሳብ ተግባራዊ የማያደርጉ አስፈፃሚ አላካት ላይ በህግ ተጠያቂ ይሆናሉ ብሏል።

በኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት በአፍሪካ ሞዴል የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ለመፍጠር እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታውቋል።

ይሁን እንጂ እቅዱን ስኬታማ ለማድረግ አስፈፃሚ አካላት ከኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም የሚሰጣቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብሏል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በቀጣይ አስር ዓመታት ሊተገብረው ባቀደው የአስር ዓመት መሪ እቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ ውይይት አድርጓል።

የተቋሙ ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሃይሌ ለኢዜአ እንዳሉት ተቋሙ ከተቋቋመበት ከአዋጅ ቁጥር 1142/2011 እና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 የሚመነጭ ስልጣን አለው።

አስፈፃሚ አካላት በዜጎች ላይ የሚያደርሱትን አስተዳደራዊ በደል በመመርመርና የመፍትሔ ሃሳብ በማቅረብ ተፈፃሚ እንዲሆን የማድረግ ስልጣንና ሀላፊነት አለበት ብለዋል።

ነገር ግን ባለፉት ዓመታት ተቋሙ ከፖለቲካና ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ነጻና ገለልተኛ መሆን ስላለቻለ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና መልካም አስተዳደር ማጎልበት የሚጠበቅበትን ያህል ማበርከት አልቻለም ብለዋል

ከለውጡ በኋላ በአንጻራዊነት ነጻና ገለልተኛ ቢሆንም አሁንም የሚቀሩ ስራዎች መኖራቸውን አመልክተዋል።

በአስር ዓመት መሪ እቅዱ በአፍሪካ ሞዴል የዴሞክራሲ ተቋማ የመሆን ህልሙን እውን ለማድረግ አስፈፃሚ አካላት የምንሰጣቸውን የመፍትሔ ሃሳቦች ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

አሁን ባለው ነባረዊ ሁኔታ ተቋሙ በአስተዳደራዊ በደሎች ላይ ከሚሰጣቸው የመፍትሄ ሃሳቦች ገቢራዊ የሚሆኑት 48 በመቶ ብቻ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ከዚህም ባለፈ አስፈፃሚ አካላት መረጃ የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው አለማወቅ ወይም እያወቁ አለመስጠት እንደ ሀገር አንድ የመረጃ ማግኛ ማዕከል ያለመኖር ችግሮች ይስተዋላሉ ብለዋል።

በመሆኑም የተቋሙን የረጅም ጊዜ እቅድ ለማሳካት አስፈፃሚ አካላት መብትና ግዴታቸውን ለይተው ለህግ ተገዥ መሆን አለባቸው፤ ከዚህ ሲያልፉም ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አቡ ብርኪ እና የፍትህ ንዑስ ኮሜቴ ሰብሳቢ አቶ አበበ ጎዴቦ፤ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስተዳደራዊ በደሎች እንዳይፈጸሙ ክትትል የማድረግ በህግ የተሰጠ ስልጣን እንዳለው አብራርተዋል።

በመሆኑም ተቋሙ በምርመራ የሚያቀርባቸውን የመፍትሄ አቅጣጫዎች አስፈፃሚ አካላት የመተግበር ግደታ አለባቸው ብለዋል።

የተቋሙን የመፍትሄ ሃሳቦች ተቀብለው ተግባራዊ የማያድርጉ ሲያጋጥሙም በህጉ መሰረት ተጠያቄ ይሆናሉ፤ ለዚሀም ምክር ቤቱ ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ብለዋል።

የፌረደራል መንግስት የአስተዳደር ተቋማት ስነ ስርዓት አዋጅ ለዚህ አጋዥ መሆኑን ገልጸው የተቋሙን የመፍትሄ ሃሳብ ገቢራዊ የማያደርጉ አስፈፃሚ አካላት ከ5 እስከ 7 ዓመት በእስራት እንደሚያስቀጣ በህጉ መደንገጉንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድምጽ በመሆን እንዲያገለግል በአዋጅ ቁጥር 1142/2011 እንደገና መሻሻሉ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም