ህብረተሰቡ ያለምንም መዘናጋት ራሱንና ሌሎችን ከኮሮና ሊጠብቅ ይገባል---የድሬዳዋ ጤና ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ ያለምንም መዘናጋት ራሱንና ሌሎችን ከኮሮና ሊጠብቅ ይገባል---የድሬዳዋ ጤና ቢሮ
ድሬዳዋ መጋቢት 16/ 2013 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እያስከተለ ያለው ጉዳት እየከፋ በመሆኑ ህብረተሰቡ ያለምንም መዘናጋት ራሱንና ሌላውን ሊጠብቅ እንደሚገባ የድሬዳዋ የጤና ቢሮ አሳሰበ።
በከተማው የኮቪድ- 19 የህክምና ማዕከል በገጠመው የኦክስጂን እጥረት ፅኑ ህመምተኛ መቀበል እንደማይችል የማዕከሉ የሃኪሞች አስተባባሪ ዶክተር ሙባረክ ሃይረዲን አስታውቀዋል፡፡
የድሬዳዋ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ እንዳስታወቁት በአስተዳደሩ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በመስፋፋቱ ጉዳቱ እየጨመረ ይገኛል፡፡
በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል።
ባሳለፍነው ሣምንት ብቻ 380 ሰዎች ተመርምረው 125ቱ ቫይረሱ እንደተገኘባቸውና የ3ት ሰዎች ህይወት ማለፉን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
"በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ከቀዳሚው ሳምንት በ40 በመቶ በላይ ጭማሬ አሳይቷል" ብለዋል፡፡
የፅኑ ህሙማን ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው በአስተዳደሩ ከፍተኛ የኦክስጂን እጥረት በመኖሩ ችግሩን አስከፊ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡
ህብረተሰቡ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ከመጠቀም ጀምሮ መከላከያ መንገዶችን ሣይዘናጋ በመተግበር ራሱን፣ ቤተሰቡንና ሀገሩን ማዳን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የፍትህና የፀጥታ አካላትም የመከላከያ መንገዶች በአግባቡ እንዲተገበሩ የጀመሩትን ቁጥጥር እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል ፡፡
በድሬዳዋ አስተዳደር የኮቪድ -19 ህክምና ማዕከል ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኘው የፈረንሣይ ሆስፒታል የኦክስጂንና መከላከያ ቬንቲሌተር እጥረት ማጋጠሙን የገለጹት ደግሞ የማዕከሉ የህክምና ባለሙያዎች አስተባባሪ ዶክተር ሙባረክ ሃይረዲን ናቸው።
በሆስፒታሉ ባለው የኦክስጂን እጥረት ፅኑ ታማሚ ተቀብሎ ለማስተናገድ የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን አመልክተዋል።
የኦክስጂን እጥረቱን ለመፍታት ከሚመረትባቸው ከተሞች ለማምጣት ቢሞከርም በወረፋ ብዛት ማግኘት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡
የጤና ባለሙያዎች ድካምና ትጋት ፍሬ የሚያፈራው ህብረተሰቡ በሽታውን ሣይዘናጋ ለመከላከል በሚያደርገው ጥንቃቄ በመሆኑ ነዋሪው ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡
በሆስፒታሉ ታክመው ካገገሙ መካከል የፒኤች ዲ ተማሪ አብይ ሰራዊት አንዱ ናቸው፡፡
ተማሪው እንደተናገሩት በኮቪድ -19 ህመም ለአንድ ወር በሆስፒታሉ በኦክስጂን ታግዘው ህይወታቸው ተርፏል፡፡
ነዋሪው ኮቪድን እንደቀላል ጉዳይ እያየው መሆኑን ተናግረው አንድም ዜጋ ለደቂቃ ያለ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ከቤቱ መውጣት እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡
"ትምህርቴን ፣ ጊዜዬን፣ ገንዘቤንና ህይወቴን አደጋ ላይ ጥሎታል፤ የህክምና ባለሙያዎች በአእምሮዬ ላይ በሰሩት ስራ ዛሬ አገግሜያለሁ፤ አሁን በኦክስጂን ከመተንፈስ አገግሜ ንፁህ አየር መሳብ ጀምሬያለሁ" ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ኮቪድ-19 ከተከሰተ ጀምሮ 30ሺህ 537 ሰዎች ተመርምረው 3ሺህ 196ቱ ቫይረሱ እንደተገኘባቸውና የ33 ሰዎች ህይወት ማለፉን ከጤና ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡