በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ስርጭት መጨመርን ተከትሎ የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያዎችን የሚጠባበቁ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ስርጭት መጨመርን ተከትሎ የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያዎችን የሚጠባበቁ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ገለጸ
መጋቢት 15፤2013 (ኢዜአ)በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ስርጭት መጨመርን ተከትሎ የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያዎችን የሚጠባበቁ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ገለጸ፡፡
የኮቪድ 19 የቫይረስ ዝርያ በየጊዜው እየተቀያየረ አሳሳቢ በሆነ ደረጃ የዓለም አገራትን እያዳረሰ መሆኑም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ከጤና ሚኒስቴርና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታትና ለመቆጣጠር መጠነ ሰፊ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል ፡፡
ኮቪድ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ አንድ አመት ያስቆጠረ ሲሆን የመጀመሪያው ክትባትም መጋቢት 4 ቀን 2013 መጀመሩ ይታወሳል፡፡
በዚህም በተለይም በደቡብ አፍሪካ፣ እንግሊዝ እና ብራዚል የተለዩ ወይም የተገኙ የኮቪድ 19 አዲስ ዝርያዎች የመተላለፍ መጠንን ጨምሮ የሚያደርሱት የሞት እና ህመም ምጣኔ ከፍተኛ መሆኑን ኢንሰቲቲዩቱ ጠቁሟል፡፡
እነዚህ ዝርያዎች በስፋት እየተሰራጩ ሲሆን በሀገራችን ካለው የየብስ እና የአየር ትራንስፖርት እንዲሁም የድንበር ግንኙነት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ተጋላጭነትን አሳድሯል፡፡
አሁን ላይ ማህበረሰቡ የሚከተለው የጥንቃቄ መንገድ መቀነስ ሃይማኖታዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መሰባሰቦች በመጨመራቸው የበሽታው ስርጭት በከፍተኛ ፍጥነት እንዲጨምር ማድረጉን ኢንስቲቲዩቱ አስታውቋል፡፡
የስርጭቱን መጨመር ተከትሎ እንክብካቤ የሚፈልጉ ህሙማን፣ የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያዎችን የሚጠባበቁ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉንም ገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የህክምና ግብዓቶች እጥረትና የኮቪድ ህከምና የሚሰጡ ማዕከላት ከአቅማቸው በላይ ሆኗል ብሏል።
በዚህም የበሽታው አሳሳቢነት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል ይላል የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት በሰጠው ማሳሰቢያ፡፡
የኮቪድ 19 ምልክቶችን የሚያሳዩና በሞት የሚለዩ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ እንደሚገኝም አመልክቷል።የበሽታው የስርጭት ምጣኔ በዓለም ጤና ድርጅት ምክረ ሃሳብ መሰረት ጠንካራ የሕብረተሰብ ጤና እና ማህበራዊ እርምጃዎችን መተግበር እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ ነውም ተብሏል፡፡
ስለሆነም ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የኮቪድ 19 በሽታን ለመቆጣጠር በወጣው መመሪያ መሰረት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ በተለይም ፣-ከዚህ በፊት ለኮቪድ 19 ዝግጁነት እና ምላሽ የተዋቀሩ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማነቃቃትና ማጠናከር፣-ሲካሄዱ የነበሩ መደበኛና መደበኛ ያልሆኑ የሕብረተሰብ ጤና ቅኝት ፣የላብራቶሪ ምርመራ፣የታማሚዎች ልየታና ህክምና፣የማህበረሰብ ተግባቦት እና ንቅናቄ ፣በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ፣የድንበር መግቢያ በሮች ቅኝት ስራ እና ተጓዳኝ ስራዎችን በትኩረት ማነቃቃትና ማጠናከር፣-የኮቪድ 19 መከላከያ መንገዶችን በመመሪያ 30/ 2013 መሰረት በሁሉም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ፣ ማህበራዊ እና ሃይማኖታዊ ቦታዎች ላይ እንዲተገበሩ ተገቢውን እገዛ ማድረግ፣-በማህበራዊ፣ ሀይማኖታዊ ፣ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ወቅት የኮቪድ 19 መከላከያ መንገዶች መተግበራቸውን ማረጋገጥና አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማከናወን፣ትኩረት የሚሹ ተቋማትንና ቦታዎች በመለየት ተገቢውን የወረርሽኝ መከላከል እና መቆጣጠር ስራዎች እንዲጠናከሩ በማድረግ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ከፍተኛ የበሽታ ስርጭት ፣ መከላከልና መቆጣጠር ስራዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲሰሩ ኢንስቲቲዩቱ አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ ሕበረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የነበረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡