ኢትዮጵያ ደመናን ወደ ዝናብ የመለወጥ ቴክኖሎጂን ገቢራዊ ማድረጓ ትልቅ ብልሃት ነው-የሳይንስ ሊቃውንት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ደመናን ወደ ዝናብ የመለወጥ ቴክኖሎጂን ገቢራዊ ማድረጓ ትልቅ ብልሃት ነው-የሳይንስ ሊቃውንት
አዲስ አበባ መጋቢት 15/2013 (ኢዜአ)ኢትዮጵያ ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂን ገቢራዊ ማድረጓ መፍትሄ የሚያመጣ ትልቅ ብልህነት ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋራገራቸው የሳይንስ ሊቃውንት ገለጹ።
በትናንትናው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ማብራሪያ ኢትዮጵያ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ጨምሮ በሳይንስ ላይ ልዩ ትኩረት ስለማድረጓ ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ የሚፈጠረውን ከፍተኛ የደመና ክምችት በሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ ወደ ዝናብ ቀይሮ ለጥቅም ማዋል ላይ ገቢራዊ ማድረግ መጀመሯን አንስተዋል።
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተፈጥሮ ሳይንስ ሊቃውንት በሳይንስና ቴክኖሎጂ የማይቻል ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።
አንጋፋው የስነ ሕይወት ተመራማሪና ፖለቲከኛው ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እንዳሉት ደመናን ወደ ዝናብ ለውጦ መጠቀም በአደጉት አገራት የተለመደ የቴክኖሎጂ ውጤት ነው።
ሳይንስ አንድም መፍጠር፣ አንድም የተፈጠረውን ተጠቅሞ የሚፈለገውን ጥቅም ማስገኘት እንደሆነ ገልጸው፤ ደመናን የማዝነብ ቴክኖሎጂ ወደ አገር ውስጥ አስገብቶ መጠቀም እንደ ኢትዮጵያ በርካታ አርሶ አደሮች ላሉት አገር ብልህነት ነው ብለዋል።
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለማበልጸግ ብዙ ጊዜና ሀብት የሚጠይቅ እንደሆነ በመግለጽ፤ በስራ ላይ የሚገኙትን ቴክኖሎጂዎች መጠቀም ትልቅ ጥበብ እንደሆነም ገልጸዋል።
በእስካሁኑም አገራችን "በዘርፉ ላይ ትኩረት ለማድረግ ተጎትታለች" የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ አሁን ላይ በዘርፉ በስፋት መስራት መጀመሩ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያም እንደሚሉት የማህበረሰብ ኑሮን ለማሻሻል፣ የአየር ንብረት ውጥን በመቋቋምና የሰው ልጅ አድካሚ ስራን ለማቃለል በቴክኖሎጂ የመቀየር ስራ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ማህበረሰብ በሁሉም ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ መስኮች መስተጋብራቸው የተሳሰረ እንደሆነ ገልጸው፤ ኢትዮጵያም በዘርፉ ላይ እምርታ እያሳየች መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም አራተኛው አብዮት የሚሰኘው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በሁሉም መስኮች የሰውን ልጆች ስራ እየተካ መምጣቱን ገልጸዋል።
'ይህም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ተፈጥሮን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ባይቻልም ተፈጥሮን ግን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተጠጋን ነው' ብለዋል።
ኢትዮጵያ ደመናን ወደ ዝናብ መቀየር መጀመሯ ትልቅ ስኬትና ወሳኝ ጥበብ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቴክኖሎጂ የማይቻል ነገር እንደሌለና በተለያዩ አገሮች የተለመደ ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ትምህርትና ባህሪ ኮሌጅ ባልደረባ ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ፣ በአሁኑ ወቅት የዓለም የምርምር ዘይቤ ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚመራበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ብለዋል።
ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና መሰረት እንደሆነ ገልጸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቴክኖሎጂ የደመና ክምችትን ወደ ዝናብ የመለወጥ ጅማሮን እውን በማድርጋቸው አድንቀዋል።
በዚህም የሳይንስ ባህል በአጠቃላይ ትምህርት ውስጥ የሚሰጠበት መንገድ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በኩል ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።