የዋጋ ግሽበት በዜጎች ላይ እያስከተለ ያለውን ችግር ለመፍታት መንግስት የጀመረውን ጥረት እንዲቀጥል ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የዋጋ ግሽበት በዜጎች ላይ እያስከተለ ያለውን ችግር ለመፍታት መንግስት የጀመረውን ጥረት እንዲቀጥል ተጠየቀ
መጋቢት 15/2013 (ኢዜአ) የዋጋ ግሽበት በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ዜጎች ላይ እያስከተለ ያለውን ችግር ለመፍታት መንግስት የጀመረውን ጥረት እንዲቀጥል ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ህዝቡ ሰላሙን ለማስጠበቅ ለጥፋት የሚሰሩ አካላትን በማጋለጥ ከመንግስት ጎን በመቆም አንድነቱን ማጠናከር ይኖርበታልም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በትናንትናው ዕለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ የዋጋ ግሽበት በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች እየፈተነ መሆኑን ገልፀዋል።
ሰው ሰራሽ እጥረት የሚፈጥሩ ነጋዴዎች፣ የምርት እጥረት እና አለም አቀፍ ሁኔታዎችም ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ምክንያቶች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ስርዓት የማስያዝ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣም እየተሰራ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
የሚታረሱ መሬቶችን በመጨመር፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርታማትን በማሳደግ እና የገበያ ሰንሰለት ችግርን በመፍታት የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ መንግስት በዘላቂነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፤ የዋጋ ግሽበት በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ዜጎች ላይ እያስከተለ ያለውን ችግር ለመፍታት መንግስት የጀመረውን ጥረት እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በተለይ ነጋዴዎች ህጋዊ መንገድን ተከትለው ኀብረተሰቡን ማገልገል እንዳለባቸውም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል።
መንግስት በአገሪቱ ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን እያከናወናቸው ያላቸው ተግባራትም ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል።
ለዚህም ስኬታማነት የህዝቡ ትብብርና እገዛ ወሳኝ በመሆኑ ከመንግስት ጎን በመሆን ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።
ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እነደሚወጡም ተናግረዋል።
ለዘንደሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከነገ ጀምሮ ለአንድ ወር እንደሚከናወን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል።