የቆዳ ኢንዱስትሪ ኢትዮጵያን ከድህነት ሊያወጡ ከሚችሉ ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስትሩ ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
የቆዳ ኢንዱስትሪ ኢትዮጵያን ከድህነት ሊያወጡ ከሚችሉ ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስትሩ ተናገሩ
አዲስ አበባ መጋቢት 15/2013 (ኢዜአ) የቆዳ ኢንዱስትሪ ኢትዮጵያን ከድህነት ሊያወጡ ከሚችሉ ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስትሩ መላኩ አለበል ተናገሩ።
የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በ2013 በጀት አመት ስምንት ወራት በቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸም ላይ ዘርፍ ከየተሰማሩ አምራቾች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ መድረኩ ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶችን ሊተካ የሚችል ምርት ማምረት መቻሉ ተገልጿል፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንዳሉት የቆዳ ኢንዱስትሪው ያልተነካ ዘርፍ ነው ።
በመሆኑም ዘርፉን ለማሳደግ የሰው ሀይል ብቃትን ማሳደግ፣ የምንዛሪ አቅርቦትን ማቃለል እና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ማድረግ ትኩረት ተደርጎበታል ብለዋል።
ዘርፉ ትልቅ ተስፋ ያለው እና በተለይም ምንም አይነት የጥሬ እቃ ግብአት የሚጠይቅ ባለመሆኑ አሟጠን መጠቀም አለብን ብለዋል።
"የቆዳ ኢንዱስትሪው ኢትዮጵያ ከድህነት የምትወጣበት አንዱ ዘርፍ ነው" ያሉት ሚንስትሩ ባለፉት ስምንት ወራት ከቆዳ ምርት ኤክስፖርት ከ26 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ዘርፉ አሁንም በሚፈለገው ደረጃ ላይ አይገኝም ያሉት ሚኒስትሩ የጥራት ችግር ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑን ጠቁመዋል።
የቆዳ ኢንዱስትሪዎች በዋናነት የሚስተዋለውን የጥራት ችግር በማሻሻል ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ሊያሳድጉ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳኛቸው ሽፈራው በበኩላቸው ባለፉት ስምንት ወራት የተገኘው ገቢ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ8 ሚሊየን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል ብለዋል።
ለዚህም የኮቪድ ወረርሽኝ ዋና ምክንያት ቢሆንም ያለንን አቅም አሟጠን አለመጠቀም ተጨማሪ ምክንያት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ለናሙና የሚቀርቡ ምርቶች እና ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ጥራት ልዩነት ያለው በመሆኑ ለግብይት እንቅፋት መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
የቆዳ ምርት አቅራቢዎችና አምራቾች የቅንጅት ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበው ጥራት ግን ለድርድር የሚቀርብ መሆን የለበትም ብለዋል።
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር በአየር ማረፊያው ቅጥር ግቢ 300 ካሬ ሜትር የመሸጫ ቦታ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በቀጣይም የመሸጫ ቦታውን ወደ 3 ሺህ ካሬ ሜተር ለማሳደግ ታስቧል ነው ያሉት።
ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመነጋገርም የውጭ ምንዛሪ ችግርን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ለአምራቾች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ቆዳን ለማለስለስ የሚያግዝ ኬሚካል በኤሊኮ-አዋሽ ፋብሪካ በመደበኛነት እየተመረተ በመሆኑ የግብዓት ጥያቄን መፍታት ተችሏል ብለዋል።
የመካከለኛና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን አቅም ለማጎልበትና ለማጠናከርም ለ156 ባለሙያዎች የከፍተኛ ትምህርት እና አጫጭር ስልጠና መሰጠቱ ተመልክቷል።
ከግብአት አቅርቦት ጋር ተያያዞ ለሚነሱ ችግሮች በየረጃው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እንዲፈቱ መደረጉም ተገልጿል።