ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክን በሰባተኛነት አጠናቀቀች

አዲስ አበባ ሀምሌ 22/2010 በአልጄሪያ በተካሄደው ሶስተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ 25 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሰባተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር አዘጋጅነት ከሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በአልጀርስ ሲካሄድ የነበረው ውድድር ትናንት ማምሻውን በተካሄደ የመዝጊያ ስነ-ስርዓት ፍጻሜ አግኝቷል። የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 18 በሆኑ ስፖርተኞች መካከል የሚካሄድ ነው። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታ በስድስት ስፖርቶች የተሳተፈች ሲሆን በአጠቃላይ ውድድሩ በ30 የስፖርት አይነቶች ተካሂዷል። አትሌቲክስ፣ ቦክስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ካራቴ፣ ብስክሌትና ጠረጴዛ ቴኒስ ኢትዮጵያ የተሳተፈችባቸው የስፖርት አይነቶች ናቸው። በዚሁ መሰረት ውድድሩ ትናንት ፍጻሜውን ሲያገኝ ኢትዮጵያ በ11 ወርቅ፣ ስምንት የብርና ስድስት የነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ 25 ሜዳሊያ በመሰብሰብ ሰባተኛ ደረጃ ይዛ ማጠናቀቋን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አስታውቋል። አትሌቲክስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ብስክሌትና ቦክስ ኢትዮጵያ ሜዳሊያ ያገኘችባቸው የስፖርት አይነቶች ናቸው። በአትሌቲክስ ዘጠኝ፣ በብስክሌት ሰባት፣ በቦክስ አምስት እንዲሁም በወርልድ ቴኳንዶ አራት ሜዳሊያ ተገኝቷል። ግብጽ በአልጄሪያ በተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ በ86 የወርቅ፣ 45 የብርና 32 የነሐስ በድምሩ 162 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አንደኛ ሆናለች። የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር (አኖካ) ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም በአልጄሪያ ባደረገው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ሌሴቶ ከአራት ዓመት በኋላ የሚካሄደውን አራተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ እንድታዘጋጅ መወሰኑ የሚታወስ ነው። ከአራት ዓመት በፊት ሁለተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ በቦትስዋና ርዕሰ-መዲና ጋቦሮኒ ሲካሄድ ኢትዮጵያ 14 የወርቅ፣ ስድስት የብር እና ሰባት የነሐስ ሜዳሊያ በማግኘት አምስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም