ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዳሴው ግድብ ላይ ያቀረቡት የመንግስት አቋም እንደሚደግፉ የአሶሳ ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዳሴው ግድብ ላይ ያቀረቡት የመንግስት አቋም እንደሚደግፉ የአሶሳ ነዋሪዎች ገለጹ
አሶሳ ፤ መጋቢት 15 / 2013(ኢዜአ) ፡-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያቀረቡት የመንግስት አቋም የሚደግፉ መሆናቸውን በአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰጡትን ማብራሪያ ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአሶሳ ነዋሪዎች እንዳሉት፤ የዶክተር አብይ አህመድ መግለጫ ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ወቅታዊ አቋም ለዓለም ያመላከተ ነው፡፡
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ደመቀ አሳዬ በተለይ በእጅጉ ያስደሰታቸው የህዳሴው ግድብ አስመልክቶ ያቀረቡት የመንግስታቸው አቋም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጪው ክረምት ሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ ውሃ መሞላቱ በምንም መልኩ እንደማይቀር መግለጻቸው ህብረተሰቡ የበለጠ በባለቤትነት እንዲደግፍ የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቀሪ የግድቡ ግንባታ በተቀመጠለት ጊዜ ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚሰጥም በግሌ ከፍተኛ እምነት አለኝ ብለዋል፡፡
ጁንታው የጠነሰሰው ሴራ የህዳሴ ግድብን ከማደናቀፍ በሻገር ኢትዮጵያን የማፍረስ እንደነበር በሃገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ አባላት ላይ የተፈጸመውን ግፍ በመጥቀስ አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ ወይዘሮ ሙሉ አልቦሮ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዳሴ ግድብ ላይ ያመላከቱት የመንግስታቸውን አቋም ከልብ እንደሚደግፉት የገለጹት አስተያየት ሰጪዋ የትኛውም የሃገር ውስጥ እና የውጭ የጥፋት ቡድኖች ተጽዕኖ ፕሮጀክቱን ለፍጻሜ ከመብቃት አያግደውም ብለዋል፡፡
ህዝቡ አንድነቱን የበለጠ በማጠናከር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ያስቀመጡት ህግን የማስከበር ስራ ዘላቂ ለማደረግ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ወጣት ፈቃዱ በየነ በበኩሉ በመጪው ክረምት የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት እንደማይቀር በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገለጸው የህልውና ጉዳይ በመሆኑ እንዲሳካ እንደሚደግፍ ተናግሯል፡፡
ፕሮጀክቱን ለማደናቀፍ ለሚጥሩትም የዶክተር አብይ አህመድ ማብራሪያው ግልጽ መልዕክት አስተላፈዋል ብሏል፡፡
በመደጋገፍ ፕሮጀክቱን ለማስፈጸም ከቦንድ ግዥ ጀምሮ የትኛውንም ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን እንደሚወጣ ገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገራዊ ጉዳይ የሰጡት ማብራሪያ የበለጠ ከጎናቸው እንድንቆም አድርጎናል ያሉት ደግሞ ሾፌር የሆኑት አቶ መስፍን ሳተናው ናቸው፡፡
የህዳሴውን ግድብ የማጠናቀቅ ቆራጥ አቋማቸውንም በመደገፍ ፕሮጀክቱን ለማደናቀፍ የሚጥሩ እንደሚቃወሙና ለዚህ ደግሞ የአካባቢቸውን ሠላም በመጠበቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
እኛን የሚያዋጣን አንድነታችንን ማጠናከር ብቻ ነው ብለዋል፡፡